ሰኔ O9/2O16 ዓ/ም [ወልቂጤ]
1 ሺህ 4 መቶ 45ኛው የኢድ-አል አድሃ [አረፋ] በዓል በወልቂጤ ከተማ በተለያዩ ሃይማኖታዊ ስርዓቶች በድምቀት ተከብሯል።

በእስልምና ዕምነት ተከታዮች ዘንድ በድምቀት ከሚከበሩ ሀይማኖታዊ በዓላት መካከል የኢድ አል አድሃ [አረፋ] በዓል አንዱ ነው፡፡
በመሆኑም 1 ሺህ 4 መቶ 45ኛው የኢድ-አል አድሃ [አረፋ] በዓል በወልቂጤ ከተማ በተለያዩ ሃይማኖታዊ ስርዓቶች በድምቀት ተከብሯል ።

የወልቂጤ ከተማ የበድረዲን መስጂድ ኢማም ኡስታዝ አብድልጀሊል ህያር ለህዝበ ሙስሊሙ የእንኳን አደረሳችሁ መልእክ ባስተላለፉበት ወቅት እንዳሉት ኢድ አል አድሃ አረፋ አላህ የነብዩ ኢብራሂምን ፍቅርና እምነት ለመፈተን ልጃቸውን ለመስዋዕትነት እንዲያቀርቡ ያዘዘበትን ዕለት ለማሰብ የሚከበር ሃይማኖታዊ በዓል ነው ብለዋል።

በዓሉን ስናከበር በጦርነት ምክንያት ቤተሰቦቻቸውን በሕይወት ያጡ ወገኖች፣ ከቤት ንብረታቸው የተፈናቀሉ ወገኖችን እንዲሁም በየአካባቢያችን የሚገኙ ሚስኪኖችን በማስታወስ በጋራ፣ በደስታ እና በፍቅር ማሳለፍ እንደሚገባም ጠቁመዋል።

የአረፋ በዓል ያለው ለሌለው እያካፈለ በአብሮነትና በመተጋገዝ እንዲሁም በመረዳዳት የሚከበር፣ እዝነት ጎልቶ በተግባር የሚታይበት ሃይማኖታዊ ክብረ በዓል መሆኑንም የበዓሉ ታዳሚዎች ገልፀዋል።
በመሆኑም አቅም የፈቀደለት ሁሉ ዕርድ ፈፅሞ በአብሮነት ተካፍሎ በመብላት የሚከናወን መሆኑን ተናግረው በዓሉ የተቸገሩትን በመርዳትና በአብሮነት እንደሚያሳልፉት ገልፀዋል።

በዓሉ በተለያዩ የእስልምና እምነት ሃይማኖታዊ ስነ ስርዓቶች በመታጀብ ነው የተከበረው፡፡

