
መጋቢት 30 /2018 ዓ.ም(ወልቂጤ)
የወልቂጤ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ጽህፈት ቤት እና ሳይንስና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ጽህፈት ቤት በጋራ በመሆን የትምህርት ቤቶች የሳይንስ የፈጠራ ስራዎች ውድድር አዘጋጅተው ማወዳደራቸው ተገለፀ።

”ሳይንስ ይመራናል ቴክኖሎጂ ያስቀድመናል” በሚል መሪ ቃል 5ኛ ዙር የትምህርት ቤቶች የ2018 ዓ.ም ማጠቃለያ የሳይንስና የፈጠራ ስራ ውድድር የተለያዩ ባለድርሻ አካላት በተገኙበት በያበሩስ አጠቃላይ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት መካሄዱ ተገለፀ።

የወልቂጤ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ጽህፈት ቤት ሀላፊ ወይዘሮ ስሜነሽ ግርማ ባደረጉት ንግግር የሳይናስና ፈጠራ ውድድር ዓላማው አንደኛ እና መካከለኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የሚገኙ መምህራን እና ተማሪዎች ፈጠራን የሚያበረታታ በትምህርት ያገኙትን በሳይንስና ፈጠራ ተጨባጭ ለማድረግ ታሳቢ ማድረጉን ተናግረው

በተማሪዎች እየተሰሩ ያሉ የፈጠራ ስራዎች የተማሪዎችን አቅም ከማጎልበት ባሻገር ወጪና ጊዜን በመቆጠብ ዘርፈ
ብዙ ፋይዳ ስላላቸው የትምህርት ተቋማት ከቀለም ትምህርት ባሻገር የሣይንስና ፈጠራ ስራ ላይ ትኩረት አድርገው ሊሰሩ እንደሚገባም አብራርተዋል።

ወይዘሮ ስሜነሽ አክለውም በሀገር ደረጃ ሰፋፊ የዲጂታላይዜሽን ስራዎች መጀመራቸውንና ይህን ለማሳደግ የተማሪዎች የፈጠራ ስራዎች ትልቅ ድርሻ እንዳላቸው ጠቁመው የፈጠራ ስራዎችን ዉጤታማ ለማድረግ በከተማው በሚገኙ ትምህርት ቤቶች የተለያዩ ድጋፎችና ስልጠናዎች ሲሰጡ መቆየቱንም ገልጸው

በተማሪዎች የቀረቡት የፈጠራ ስራ ውጤቶች ተስፋ ሰጪ በመሆናቸው የበለጠ ዳብረው እንዲቀጥሉ ተማሪዎች በትምህርታቸውና በፈጠራ ስራው ላይ ውጤታማ እንዲሆኑ ጊዜያቸውን በዋዛ ፈዛዛ ከማባከን ተቆጥበዉ ለአዳዲስ የስራ ፈጠራና የራስ ክህሎት ማጎልበቻ እንዲህ አይነቱ ዝግጅት ተነሳሽነትን የሚጨምር ነዉ ብለዋል::

የወልቂጤ ከተማ አስተዳደር ሳይንስና ቴክኖሎጂ ጽህፈት ቤት ሀላፊ የሆኑት አቶ ሀምዱ ካሚል በበኩላቸው ለሳይንስና የፈጠራ ስራዎች ልዩ ትኩረት በመስጠት የፈጠራና ቴክኖሎጂ ዘርፉን ይበልጥ ማሳደግ እንደሚያስፈልግ የገለፁ ሲሆን

በዓለማችን የበለፀጉ ሀገራት ሚስጥር የሳይንስና ፈጠራ ስራዎች ዉጤት እና ለዘርፉ የሰጡት ልዩ ትኩረት መሆኑን ያነሱት አቶ ሀምዱ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ለአንድ ሀገር ሁለንተናዊ ዕድገት ቁልፍ ሚና እንዳለው አስታውሰዋል።

አቶ ሀምዱ አያይየዘውም የዛሬው መርሀግብር የተማሪዎችን የፈጠራ ክህሎት ለማሳደግ፣ ልምድ ለመጋራትና ስራዎቻቸውን ለማስተዋወቅ ትልቅ እድል የሚፈጥር መሆኑን አመላክተው ከአሁን በኋላም የተማሪዎችን የፈጠራ አቅም የሚያጎለብቱ መርሃ ግብሮች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ገልጸዋል፡፡

አሁናዊው አለም ሁሉም ዘርፎች ዲጂታላይዝ እየሆኑ የመጡበት መሆኑን በመረዳት ተገልጋዩንም አገልጋዩንም በቴክኖሎጂው ዘርፍ በሚገባ ማብቃት እንደሚያስፈልግ አቶ ሀምዱ አስታውቀዋል።

እንደሃገር ብልጽግናን ለማራጋገጥ ትኩረት ከተሰጣቸው የሃገር በቀል ኢኮኖሚ ሪፎርም ውስጥ አንዱ የሳይንስና ኢኖቬሽን ዘርፍ ነውም ብለዋል።

በዕለቱም የተለያዩ የፈጠራ ውጤቶች ያዘጋጁ ተማሪዎች የፈጠራ ስራቸውን ምንነት÷ ዓላማና ጠቀሜታ ለጎብኚዎች አስረድተዋል።

አንዳንድ የፈጠራ ስራ ባለቤቶች በሰጡት አስተያየት ንድፈ ሀሳቦችን ከተግባር ትምህርት ጋር በማቀናጀት የተማሪዎችን የመፍጠር አቅም ለማሳደግ የተጀመረው ጥረት የሚመለከተው አካል አጠናክሮ ሊቀጥልበት ይገባል ብለዋል።

በዕለቱ መርሀግብር የጉራጌ ዞን ሳይንስና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ መምሪያ ሀላፊ አቶ ደምስ ገብሬ÷ ጉራጌ ዞን ትምህርት መምሪያ ሀላፊ አቶ መብራቴ ወልደማረያም ÷የወልቂጤ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ጽህፈት ቤት ሀላፊ ÷ የወልቂጤ ከተማ አስተዳደር ሳይንስና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ጽህፈት ቤት ሀላፊና የከተማ አስተዳደር የስራ ኃላፊዎች የሁለቱ ተቋማት ባለሙያዎች ተሳትፈውበታል።

በስተመጨረሻም በ6ኛ፣በ8ኛ እና በ12ኛ ክፍል ተማሪዎች የጥያቄና መልስ ውድድር የተካሄደ ሲሆን በፈጠራ ስራውም ከ1-3 ለወጡት ማበረታቻ ሽልማት ተበርክቶላቸዋል።

