ወልቂጤ፣ ህዳር 13/2019 ዓ.ም
የያበሩስ አጠቃላይ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የ1980ዎቹ ተማሪዎች ማህበር 2ኛ ዓመት የምስረታ በዓሉን በመቄዶኒያ የአረጋውያንና የአእምሮ ህሙማን መርጃ ማዕከል ወልቂጤ ቅርንጫፍ በምሳ ማብላት መርሃ ግብር አከበሯል።

በመርሃ ግብሩ የተገኙት በጉራጌ ዞን የወልቂጤ ከተማ ሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ወይዘሮ ፈቲሃ አባድር፣ በማዕከሉ የሚገኙ አረጋውያንና አቅመ ደካሞች የማኅበረሰቡን ድጋፍና እንክብካቤ እንደሚሹ ገልጸው፣ ሁሉም የማኅበረሰብ ክፍል በቻለው አቅም ድጋፍ እንዲያደርግ ጥሪ አቅርበዋል።
ኃላፊዋ ዜጎች ልደትን፣ ሠርግንና የተለያዩ ሃይማኖታዊ በዓላትን በማዕከሉ ከአረጋውያኑ ጋር በማክበር ደስታቸውን እንዲጋሩ፣ ተማሪዎችም በክበባት ተደራጅተው በቅዳሜና እሁድ የእረፍት ጊዜያቸው ወደ ማዕከሉ በመምጣት የአቅመ ደካሞችን እንክብካቤ እንዲያግዙ አሳስበዋል።
ባለሀብቶች የንጽህና መጠበቂያ ቁሳቁሶችን እንዲያቀርቡ፣ የማኅበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚዎችም ማዕከሉን በመጎብኘትና በማስተዋወቅ ድጋፍ እንዲያሰባስቡ ጠይቀዋል። የቀድሞ ተማሪዎቹን ተግባርም ለሌሎች አርዓያ እንደሆነ አድንቀዋል።

የማኅበሩ ሰብሳቢ አቶ ያለው ባረጋ በበኩላቸው፣ ማኅበሩ በ1980ዎቹ በጎሮ (አበሩስ) አጠቃላይ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተምረው የተመረቁና በሀገር ውስጥና በውጭ ሀገር በተለያዩ የሥራ ዘርፎች የተሰማሩ 25 አባላትን ያቀፈ መሆኑን ገልጸዋል።
ማኅበሩ ጳጉሜ 3 ቀን 2016 ዓ.ም ከተመሠረተ ጀምሮ ከአባላቱ በሚሰበስበው መዋጮ በወልቂጤ ከተማ የሚገኙ አረጋውያንን፣ አቅመ ደካሞችን፣ አካል ጉዳተኞችንና በጎዳና ላይ የሚኖሩ ሕፃናትን ለመደገፍ እየሠራ መሆኑን አስረድተዋል።

ወደፊትም ከማዕከሉ ጎን በመቆም ድጋፉን እንደሚቀጥሉ አረጋግጠዋል።
የማኅበሩ ጸሐፊ ወይዘሮ ሕይወት መኮንን እንደገለጹት፣ ማኅበሩ በአሜሪካ በሚኖሩት የቀድሞ ተማሪ ዶክተር ጅላሉ አስመራና በሌሎች አባላት አነሳሽነት የተመሠረተ ሲሆን፣ አረጋውያንን በዘላቂነት ለመደገፍና አካል ጉዳተኞች የድጋፍ ቁሳቁስ እንዲያገኙ ፕሮጀክት ቀርጾ ወደ ተግባር ለመግባት እየሠራ ነው ብለዋል።
የዛሬው የምሳ ማብላት መርሃ ግብርም ሌሎች የማኅበረሰብ ክፍሎች ማዕከሉን በመጎብኘት ድጋፍ እንዲያደርጉ ለማነሳሳት ያለመ መሆኑን ጠቁመዋል።

