
ስፖርታዊ ውድድሮች ክልላዊ አንድነትና የእርስ በርስ ትስስር ይበልጥ እንዲጠናከር ያደርጋሉ፦ ዶ/ር ንጉሴ አስረስ
የካቲት 10/2018(ወልቂጤ)
3ኛው የማእከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ልዩ ልዩ ሻምፒዮና፣ የባህል ስፖርቶች ውድድርና ፌስቲቫል የማስጀመሪያ መረሀ ግብር በጉራጌ ዞን በወልቂጤ ከተማ በይፋ ተጀምሯል።
የማእከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ርእሰ መስተዳድር ልዩ አማካሪ ዶ/ር ንጉሴ አስረስ እንደተናገሩት ስፖርት ህብረ ብሄራዊ አንድነት ለማጠናከር፣ የወንድማማችነትና የእህትማማችነት መንፈስ ለመፍጠር እንዲሁም ሀገራዊ ትርክትን ለመገንባት ወሳኝነት አለው።
በክልሉ በስፖርት ልማቱ ወጣቱን ተሳታፊና ተጠቃሚ ለማድረግ የስፖርት መሰረተ ልማት እንዲሟሉ በማድረግ በሀገር አቀፍ ደረጃ አበረታች ውጤቶች ማምጣት ተችሏል ብለዋል።
ስፖርታዊ ውድድሮች ክልላዊ አንድነትና የእርስ በርስ ትስስር ይበልጥ እንዲጠናከር ያደርጋሉ ብለዋል ልዩ አማካሪው።
ዶክተር ንጉሴ አክለውም ውድድሩ በሰላም እንዲጠናቀቅ ስፖርተኞች ፣ዳኞች፣አሰልጣኞች፣ ቡድን መሪዎች፣ደጋፊዎች እና የጸጥታ አካላት የበኩላቸው እንዲወጡ አሳስበዋል።

የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ኃላፊ አቶ ጌታቸው ሌሊሾ በክልሉ በባለፉት አመታት የክልሉ የስፖርት ልማትን በተሻለና ወደ ላቀ ደረጃ ለማድረስ በሁሉም መስክ ብቁ ንቁና በስነምግባር የታነጸ፣ ተወዳዳሪ ስፖርተኞች ለማፍራት በትኩረት እየተሰራ ይገኛል ብለዋል።
ለተከታታይ 10 ቀናት በወልቂጤ ከተማ የሚካሄደው 3ኛ ዙር የክልሉ ልዩ ልዩ ስፖርት ሻምፒዮናና የባህል ስፖርት ውድድር የክልሉ ገጽታ ከመገንባት ባለፈ ክልሉ የሚወክሉ ተተኪ ስፖርተኞችን ማፍራት፣ ወንድማማችነትና እህትማማችነት ለማጠናከር ፋይዳው ትልቅ ነው ብለዋል።
በዚህ ውድድር በ27 የስፖርት አይነቶች ከ2ሺ 66 ሉኡካን ቡድኖች ይሳተፋሉ ነው ያሉት።
ውድድሩ ተጀምሮ እስኪጠናቀቅ በስፖርታዊ ጨዋነት፣ በወዳጅነት፣ በመቻቻል፣ በመከባበር፣ በአብሮነትና የእርስ በእርስ በመተዋወቅ ሊሆን ይገባል ሲሉ አቶ ጌታቸው መልእክት አስተላልፏል።

የጉራጌ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ክቡር አቶ ላጫ ጋሩማ መላው የክልላችን የስፖርት ልኡካን ቡድን የእንግዳ ተቀባዩ የጉራጌ ማህበረሰብ ውስጥ እና የአብሮነት ተምሳሌት የሆነችው ትንሿ ኢትዮጵያ ወደ ሆነችው ወልቂጤ ከተማ እንኳን ደህና መጣችሁ ሲሉ ምኞታቸው አስተላልፏል።
ስፖርታዊ ውድድሮች የክልላችን ማህበረሰብ እና በተለይ ወጣቶች የእርስ በርስ ግንኙነታቸው እንዲጠናከር ከፍተኛ ሚና ይጫወታል ብለዋል አቶ ላጫ።

አክለውም ስፖርት ጤንነቱ የተጠበቀ አምራች ዜጋ እና በስነ ምግባር የታነጸ ትውልድ ለመፍጠር ጉልህ ሚና ስላለው የዞኑ መንግስትም በትኩረት እየሰራ እንደሚገኝ ጠቁመዋል።
በመሆኑም ይህን ክልል አቀፍ ስፖርታዊ ውድድር ለመሳተፍ ወደ ከተማው የሚመጡ እንግዶች በሙሉ ሠላምና ደህንነታቸው የተጠበቀ፣ ምቹ እና አይረሴ ጊዜ እንዲያሳልፉ በቂ ዝግጅት ተደርጓል ሲሉ አቶ ላጫ ጋሩማ ገልጸዋል።

