
መጋቢት 6/2018ዓ.ም(ወልቂጤ)
ኤያና ኢንዱስትሪ መንደር ለመገንባት በጉራጌ ዞን ወልቂጤ ከተማ አስተዳደር ጋሶሬ ቀበሌ የመሰረተ ድንጋይ ተቀመጠ።
በተለያዩ 10 የኢንቨስትመንት መስኮች ለማልማት የተደራጁ አልሚ ባለሀብቶች 22,820 ካሬ/2.282/ሄክታ መሬት የወልቂጤ ከተማ ከንቲባ አቶ ሙራድ ከድርን ጨምሮ ሌሎች የስራ ኃላፊች በተገኘበት ለባለሀብቶች ርክክብ ተፈፅሟል።
ባለሀብቶቹ 2.295 ቢሊዮን የኢትዮጵያ ብር ካፒታል ማስመዝገባቸውንም ተገልጿል።
በርክክቡ ወቅት የተገኙት የወልቂጤ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ሙራድ ከድር እንደገለፁት የመደመር መንግስት እሳቤዎችን እውን ለማድረግና የከተማችን ህዝብ የብልፅግና ጉዞ ለማፋጠን ክትመትና ኢንዱስትሪን ማስፋፋት ላይ በልዩ ትኩረት እየሰራን ነው።
ከዚህ በፊት ለኢንደስሪና ለክትመት የሚገባውን ትኩረት ባለመሰጠቱ ችግሮች ሳይቀረፍ መቆየቱን አውስተው ይህ ትልቅ ፕሮጀክት መሬት ላይ ሲወርድ ለወጣቱ የሰራ እድል ከመፍጠሩም ባላይ ለአካባቢው ማህበረሰብ ኢኮኖሚ መነቃቃትና ከተሜነትን በማሳደግ ረገድ ትልቅ ሚና ይጫወታል፣ ስለሆነም ባለሀብቶቹ የወሰዱትን ቦታ በፍጥነት ወደ ተግባር መለወጥ እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።
የአካባቢው ማህበረሰብ የተለመደው ልማት ወዳድነቱን ሊያስቀጥል ይገባል ያሉት አቶ ሙራድ ባለሀብቶቹ ወደ ተግባር ሲገቡ ህብረተሰቡ ከጎናቸው ሊቆምና ሊያግዝ እንደሚገባ አብራርተዋል።

የጉራጌ ዞን የኢንቨስትመንት መምሪያ ሀላፊ ወይዘሮ አመተሩፍ ሁሴን እንዳሉት የአንድን ሀገር ኢኮኖሚ ለማረጋገጥ የግሉ ዘርፍ ያለውን ሚና አውስተው የዞኑ መንግሥት ለግሉ ዘርፍ ትኩረት በመሥጠት በርካታ ስራዎች እየሰራ እንደሚገኝ አብራርተዋል።
በሃገር ደረጃ በርካታ አስተዋጽኦ እያበረከቱ የሚገኙ ኢንድስትሪዎች በዞናችን ይገኛሉ ያሉት ኃላፊዋ እሱን በማስቀጠል የሀገራችን ብልፅግና ለማረጋገጥ በተደራጀ መልኩ እየተሰራ እንደሆነም ገልፀዋል።
የወልቂጤ ከተማ ማዘጋጃ ቤታአዊ አገልግሎት ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ቶፊቅ ሱልጣን በበኩላቸው የመሬት ርክክቡ የተፈፀመው ከዚህ ቀደም በአገልግሎት ዘርፍ ለተሰማሩና እውቅና ለተሰጣቸው በ10 የኢንቨስትመንት ኘሮጀክቶች እንዲያለሙ መሆኑን በመግለፅ አሰራሩም እንደ ክልልም ሆነ እንደ ሀገር ለኢንቨስመንት የተቀመጠውን አቅጣጫ በመከተል መሆኑን አብራርተዋል።

ርክክብ የተደረገው የኢንድስትሪ ዘርፍ አይነቶች የቆርቆሮ እና ሚስማር ማምረቻ፣ለአማራጭ ዘርፍ ሀይል፣ጨርቃ ጨርቅ ማምረቻ፣ሣሙና ፋብሪካ፣ቺፑድ ፋብሪካ፣ የህክምና ላብራቶሪ መገልገያ እቃዎች ማምረቻ ፋብሪካ፣አትክልትና ፍራፍሬ ማቀነባበሪያ፣ ምግብ ማቀነባበሪያ፣ የፕላስቲክ ውጤቶችና ጆንያ ማምረቻ እንዲሁም የጉራጌ ዞን መምህራን ማህበር የገበያ ማእከል መሆኑንም ገልፀዋል።
አቶ ቶፊቅ አያይዘውም ለማልማት ዝግጁ የሆኑ ባለሀብቶች ወደ ከተማችን ቢመጡ ምቹ የሆነ የኢንቨስትመንት አገልግሎቶች መኖራቸውን ገልፀው ከተማዋን እንዲያለሙ ጥሪ አቅርበዋል።

በኤያና ኢንዱስትሪ ማዕከል መሬቱን ከተረከቡት አልሚ ባለህቶች ውስጥ አቶ ፈድሉ በደዊና ወይዘሮ አምሳለ ባረጋ እንደገለፁት ጥያቄው ለረዥም ጊዜ ሲጠየቅ የነበረ ጥያቄ በመሆኑና በዛሬው እለት ችግሩ ተፈቶ በመረከባቸው በጣም ደስተኛ መሆናቸውን ገልፀው
ከዚህ በፊት የነበረውን የመልካም አስተዳደር ችግር የተቀረፈበትና ጥያቄዎች የተመለሰበት መሆኑን አውስተው ለኢንቬስትመንት መነቃቃት ምቹ ሁኔታዎች በማመቻቸት የአካባቢው ማህበረሰብ ወደ ትውልድ መንደሩ መጥቶ እንዲያለማ የሚያነሳሳ ነው ብለዋል ።
በርክክቡ ወቅት የወልቂጤ ከተማ ብልጽግና ፓርቲ ቅ/ጽ/ቤት የአደረጃጀት ዘርፍ ሀላፊና ረዳት የመንግስት ተጠሪ አቶ ሰፋ ዘይኑ፣ የጉራጌ ዞን ከተማ ልመትና ኮንስትራክሽን መምሪያ ሀላፊ ተወካይ አቶ ይብጌታ ንጋ፣ የወልቂጤ ከተማ አስተዳደር አመራሮች፣ የማህበራት ተወካዮች እንዲሁም የአካባቢው ማህበረሰብ ተገኝተዋል።

