ኢትዮ ኮደርስ ስልጠና ማህበረሰቡን በቴክኖሎጂ የተደገፈ እውቀትና ክህሎት ከማሳደግ ባሻገር የስራ ዕድል ከመፍጠር አኳያ ጉልህ ሚና እንዳለው ተገለፀ።

ወልቂጤ ፤ ነሐሴ12 /2017 ዓ.ም
በጉራጌ ዞን የወልቂጤ ከተማ አስተዳደር “የ5 ሚሊዮን የኢትዮጵያ ኮደርስ” ኢኒሼቲቭ ስልጠና እንቅስቃሴ ያለበት ደረጃ ተገመገመ።
የወልቂጤ ከተማ አስተዳደር ኢትዮ ኮደርስ አብይ ኮሚቴ በከተማው ያለውን “የ5 ሚሊዮን የኢትዮጵያ ኮደርስ” ስልጠና አፈጻጸም በመገምገም ቀጣይ አቅጣጫዎችን አስቀምጧል።
የኢትዮጵያ መንግሥት ከተባበሩት አረብ ኢምሬት ጋር በመተባበር ለ5 ሚሊዮን ኢትዮጵያዊን በተለያዩ የሙያ ዘርፎች የዲጂታል እውቀትና ክህሎት እንዲያዳብሩ ታስቦ የተጀመረው ስልጠና በከተማው በትኩረት እየተከናወነ እንደሚገኝ የወልቂጤ ከተማ አስተዳደር ም/ከንቲባና ጤና ጽ/ቤት ሀላፊ አቶ ሙባሪክ ዘይኑ ገልጸዋል።

በከተማው የዲጂታል ቴክኖሎጂ ሽግግር እያደገ መምጣቱን የጠቆሙት ኃላፊው በዚህም ስልጠናውን ለመከታተል የሚመዘገቡ ዜጎች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መምጣቱን ተናግረዋል።
በዚህም በከተማው ያሉ የተለያዩ የስልጠና ማዕከላትን በማቀናጀት ዜጎች የዕድሉ ተጠቃሚ እንዲሆኑ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
ከከተማው ስራ አስፈጻሚ ጀምሮ በየደረጃው ያለው አመራሮች ለዲጂታል ቴክኖሎጂ ዘርፍ መጎልበት እያሳዩት ያለው ቁርጠኝነትና ተነሳሽነት የሚበረታታ መሆኑንም አቶ ሙባሪክ ተናግረዋል።
የኮደርስ ስልጠናው የዜጎችን የዲጂታል እውቀትና ክህሎት በማሳደግ ዜጎች በዚህ ተለዋዋጭ አለም ተወዳዳሪና ብቁ ሆነው ስራ እንዲፈጥሩ እና ተጨማሪ ገቢ እንዲያገኙ እንደሚያስችል የጠቆሙት የከተማ አስተዳደሩ ሳይንስና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ጽ/ቤት ሀላፊ አቶ ሀምዱ ካሚል ገልፀዋል ።

በ 3 ዓመታት በከተማው 4ሺህ9 መቶ 51 ዜጎችን በማሰልጠንና ሰርተፊኬት እንዲያገኙ
የማድረግ ስራ የታቀደ ቢሆንም ለተግባሩ ልዩ ትኩረት በመስጠት ከ5324 በላይ ዜጎችን በማሰልጠን ሰርተፊኬት እንዲያገኙ ተደርጓል።
በተጨማሪ ለ2018 በጀት አመት 8034 ዜጎችን ለማሰልጠንና ሰርቲፋይ እንዲያገኙ ለማድረግና ፈጠራ ላይ እንዲሰማሩ ለማድረግ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን አቶ ሀምዱ አመልክተዋል።

የከተማ አስተዳደሩ የፐፕሊክ ሰርቪስና ሰው ሀብት ጽ/ቤት ሀላፊ አቶ ግርማ ንቅበሸዋ የኢትዮ ኮደርስ ስልጠና መስኮች የከተማው በርካታ ፐፕሊክ ሰርቫንት በብቃት በማጠናቀቅ ወደ ዲጂታሉ ዓለም መቀላቀላቸውን አውስተው በቀጣይ ቀሪ ፈጻሚዎችን ሙሉ በማሳተፍና ተግባሩን በልዩ ትኩረት እንደሚመሩት መልዕክት አስተላልፈዋል።
ዜጎች ሰልጥነው ከዘርፉ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ግንዛቤ ከመፈጠር ጀምሮ በከተማው የተጀመሩ ተግባራት ተጠናክረው እንዲቀጥልም ሀላፊው አሳስበዋል።
የዲጂታል እውቀት፥ ሀብት ለመፍጠርና ከመንግሥት ለዜጎች የሚሰጠውን እንዲሁም በግሉ ዘርፍ የሚቀርበውን አግልግሎት ፈጣንና ቀልጣፋ በማድረግ ጊዜና ገንዘብ የሚቆጥብ በመሆኑ ተግባሩን በጋራ ትብብር አጠናከረው እንደሚቀጥሉም ነው የኮሚቴው አካላት የገለጹት።

የኮዲንግ መሠረታዊ ክህሎት ለማዳበር የሚያስችለውን ነጻ የኦንላይን ሥልጠና እድሎች ተጠቃሚ ለመሆን https://ethiocoders.et/ በዚህ ሊንክ ላይ ይመዝገቡ።

