ቡና በስፋት በማምረታቸው ከራሳቸው ፍጆታ ባለፈ ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚ መሆናቸውን በጉራጌ ዞን ቸሃ ወረዳ የውረር በር ቀበሌ ቡና አምራች አርሶ አደር ሸዋለም አቅነዳ ተናገሩ።

የአርሶ አደሩን ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ ሁለንተናዊ ተጠቃሚነታቸውን ለማረጋገጥ ሁሉም የድርሻውን ሚና ሊወጣ እንደሚገባ ተገለጸ።

አርሶ አደር ሸዋለም አቅነዳ በቸሃ ወረዳ ውረርበር ቀበሌ ቡና አምራች አርሶ አደር ሲሆኑ ቡና ማምረት ከራስ አልፎ ለሀገር ከፍተኛ ጠቀሜታ እንዳለው ጠቅሰው በዚህም ከራሳቸው ፍጆታ ባለፈ ለማዕከላዊ ገበያ በማቅረብ ልጆቻቸው እያስተማሩ እንደሚገኙ አንስተዋል።

ምርትና ምርታማነታቸውን ለማሳደግ የተሻሻለ ዝርያ ከመትከል፣ የቡና እንክብካቤ ከማድረግ ባለፈ በሽታ በሚከሰትበት ወቅት ከባለሙያ የሚሰጣቸውን ምክረሃሳብ ተጠቅመው እየሰሩ መሆኑን ጠቅሰዋል።

የአካባቢው አርሶ አደር ያመረቱትን ምርት በጋራ በማህበር በመደራጀት ለማዕከላዊ ገበያ እያቀረቡ እንደሆነ ገልጸዋል።

የአርሶ አደሩን ምርትና ምርታማነት እንዲያድግ የሚመለከታቸው አካላት ድጋፍና ክትትል እንዲጠናከርም ጠይቀዋል።

በቸሃ ወረዳ ግብርና ጽህፉት ቤት የቡና ልማትና ጥበቃ ቡድን ዳይሬክቶሬት አቶ ዮሀንስ ጴጥሮስ በወረዳው 8ሺህ 3 መቶ 36 ሄክታር መሬት በቡና መሸፈኑን ገልጸው በዚህም ከ33 ሺህ በላይ ኩንታል ምርት ይጠበቃልም ብለዋል።

በዘንድሮ አመት 7መቶ ሄክታር መሬት ላይ ቡና ለመትከል መታቀዱንም ጠቁመው ለዚህም 2 ነጥብ 5 ሚሊዮን ችግኞችን በመንግስትና በአርሶ አደር ጓሮ መዘጋጀቱንም ጠቁመዋል።

አርሶ አደሩ በጓሮው የተሻሻሉ የቡና ዝርያ እንዲያዘጋጁ ከማድረግ ባለፈ መንግስት ከሌሎች አካባቢዎች በአካባቢው ከዚህ በፊት ተሞክረው ውጤታማ የሆኑ ችግኞችን በግዢ ለአርሶ አደሩ እንደሚቀርብም አንስተዋል።

እንደ አርሶ አደሩ በዘርፉ ውጤታማ እንዲሆኑ ባለሙያዎች በየጊዜው ድጋፍ እያደረጉላቸው እንደሚገኙ አመላክተዋል።

የአርሶ አደሩ ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ የጅማ ግብርና ምርምር ማዕከል እንሰት ከቡና ጋር በስብጥር እንዲለማ እየሰራ እንደሚገኝ ያነሱት አቶ ዮሀንስ ማዕከሉ የቡና በሽታ መከላከል ላይ በትኩረት እንዲሰራም ጠይቀዋል።

በቡና ዘርፍ የአርሶ አደሩን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ሁሉም የድርሻውን ሚና ሊወጣ እንደሚገባ ተናግረዋል ሲል የዘገበው የጉራጌ ዞን የመንግስት ኮሚዩኒኬሽን መምሪያ ነው።

Previous የጉራጌ ዞን ልማት እና እድገት ለማረጋገጥ መንግስት ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን ትኩረት ሰጥቶ መስራት እንዳለበት የዞኑ ነዋሪዎች ተናገሩ

1 Comment

  • lidiya kamil
    February 13, 2024

    Fantastic

Leave Your Comment

የቋንቋ አማራጭ

🇺🇸 English
🇪🇹 አማርኛ
🇪🇹 Afan Oromo