የጉራጌ ዞን ልማት እና እድገት ለማረጋገጥ መንግስት ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን ትኩረት ሰጥቶ መስራት እንዳለበት የዞኑ ነዋሪዎች ተናገሩ

የጉራጌ ዞን ልማት እና እድገት ለማረጋገጥ መንግስት ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን ትኩረት ሰጥቶ መስራት እንዳለበት የዞኑ ነዋሪዎች ተናገሩ።

“በአዲስ ምራፍ አዲስ ተስፋ ለአዲስ ክልል” በሚል መሪ ቃል በጉራጌ ዞን ከማህበረሰቡ ከተወጣጡ አካላት ጋር የህዝብ የውይይት መድረክ በወልቂጤ ከተማ ተካሄደ።

የውይይቱ ተሳታፊዎች እንዳሉት ጉራጌ ስራ ወዳድ፣ ሰላም ፈላጊ ከመንግስት ጋር በጋራ የሚሰራ ታላቅ የሀገር ባለ ውለታ ነው።

ቢሆንም ግን የዞኑ ልማትና እድገት ለማደናቀፍ እና ህዝቡ በመንግስት ላይ እምነት እንዳይኖረው የሚሰሩ፣ በተለይም በዞኑ በተለያዩ ወረዳዎችና ወልቂጤ ከተማ ላይ ሰላም እንዳይሰፍን በሚሰሩ ግለሰሰዎች ላይ መንግስት ህጋዊ እርምጃ መውሰድ አለበት ብለዋል።

ዞኑ ያሉትን ሀብቶች ወደ ልማት በመቀየር ህብረተሰቡ ተጠቃሚ ማድረግ ይገባል ያሉት ተሳታፊዎቹ በተለያዩ ቦታዎች ለጸጥታ ችግር መፈጠር ምክንያት የሆኑ ጉዳዮች ለይቶ ዘላቂ መፍትሄ ሊሰጣቸው ይገባል ብለዋል።

በእኖር ኤነር መገር ወረዳ ቆሴ ዙሪያና በወልቂጤ ከተማ ላይ የሚስተዋለው የፕላን ጥሰት የአካባቢው ሀብት ወደ ልማት እንዳይቀየር ከማድረግ ባለፈ ለጸጥታ ችግር መፈጠር ምክንያት በመሆናቸው የክልሉ መንግስት እልባት መስጠት ይጠበቅበታል ብለዋል።

የጉራጌ ዞን መቀመጫ ወልቂጤ በሰላምና በፍቅር የምትታወቅ፣ በማእከላዊ ኢትዩጵያ ክልልም የልማትና የንግድ ኮሪደር ከተማ አንዷ ስትሆን ብዙ ብሄር ብሄረሰቦች በእኩልነት እየኖሩባት ትገኛለች ብለዋል ነዋሪዎቹ።

በመሆኑም በወልቂጤ ከተማ ጨምሮ የዞኑ አንድ አንድ አካባቢዎች ሰላም እንዳይሆኑ እና ህዝቡን ከመንግስት ጋር ለማለያየት የሚፈልጉ አካላት መንግስት ህጋዊ እርምጃ መውሰድ እንዲሁም ሰላም የማስፈንና የህግ ማስከበር ተግባር ትኩረት ሰጥቶ መስራት እንዳለበት ጠይቀዋል።

በየ አካባቢው ከፍተኛ የሆነ የመንገድ፣ የውሃ፣ የትምህርት፣ የጤና፣ የስራ አጥነት እና ሌሎች ችግሮች የሚስተዋሉ ሲሆን መንግስት እነዚህ ጥያቄዎች ደረጃ በደረጃ እንዲፈታ የጠየቁት ነዋሪዎቹ የመብራት ዲስትሪክት እና የደም ባንክ አገልግሎት የሚሰጡ ተቋማት መገንባት እንደሚገባ ገልጸዋል።

በዞኑ ያሉ ጸጋዎች በአግባቡ በመጠቀም ከመንግስት ጎን ሆነው ዞኑ ብሎም ክልሉ እንዲለማ በጋራ እንደሚሰሩ ነዋሪዎቹ አመላክተዋል።

የክልሉ ስራ እድል ፈጠራና ኢንተርፕራይዞች ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ቶፊቅ ጁሀር የመወያያ ሰነዱን ባቀረቡበት ወቅት እንደገለፁት አዲሱ ክልል በግብርናው፣ በቱሪዝም፣ በኢንዱስትሪው፣ በኢንቨስትመንት፣ በሰው ሀይል፣ በባህላዊና ሀይማኖታዊ ሁነቶች እና ሌሎችም ያሉን ጸጋዎቻችን አሟጠን ከተጠቀምን ክልሉ በአጭር ጊዜ ማሳደግ ይቻላል ነው ያሉት።

የጉራጌ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ላጫ ጋሩማ በዚህ ወቅት እንደተናገሩት በዞኑ በርካታ የመሰረተ ልማት ጥያቄዎች ያሉ ሲሆን በዞኑ ያሉ ጸጋዎች በአግባቡ በመጠቀም ጥያቄዎቹ ደረጃ በደረጃ ለመመለስ በቀጣይ ይሰራል ሲሉ ተናግረዋል።

በአፋጣኝ እንዲመለሱ የተጠየቁት የደም ባንክ አገልግሎትና የመብራት ዲስትሪክት በዞኑ እንዲኖር ከፌደራል መንግስት ጋር እየተሰራበት እንደሆነ በመጠቆም።

ሰላም ወዳዱ፣ ሰርቶ አዳሪው፣ ሀገርን በኢኮኖሚ የገነባ፣ ከመንግሰት ጎን በጋራ የሚሰራው የጉራጌ ህዝብ ላይ አሁን አሁን የስም ማጥፋት ዘመቻ የሚያደረጉ አካላት እንዳሉ የጠቆሙት አቶ ላጫ ጉራጌና መንግስት ከዚህ ቀደምም ሆነ በቀጣይም ሳይነጣጠሉ አንድ ሆነው የሚሰሩ መሆናቸው አብራርተዋል።

የዞኑ መቀመጫ ወልቂጤ ከተማ ለዘመናት በዞኑ የምትተዳደር ከተማ ናት። የከተማው ማስተር ፕላን ከጸደቀ የቆየ ቢሆንም የፕላን ጥሰቱ ለማሰረተካከል በቅድሚያ የከተማዋ ሰላም ማረጋገጥ አስፈላጊ በመሆኑ ህብረተሰቡ ለከተማው ሰላም አስፈላጊውን ድጋፍ ማድረግ ይጠበቅበታል ብለዋል።

ይህንን ተግባራዊ ለማድረግም የክልሉ መንግስት ኃላፊነቱ ወስዶ እየሰራ እንደሆነ አስገንዘበዋል።

አቶ ላጫ አክለውም ከተማዋ ብታድግ በከተማው ያሉ ብሄረሰቦች ተጠቃሚ የሚያደርግ ነው እንጂ ማንንም ለመጉዳት አላማ ያለው እንዳልሆነ አስገንዝበዋል።

በምክትል ርእሰ መስተዳደር ማዕረግ የማእከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ትራንስፖርትና መንገድ ልማት ቢሮ ኃላፊ ዶ/ር መሀመድ ኑሪዬ በበኩላቸው የሚነሱ የመሰረተ ልማት ጥያቄዎች በፍትሀዊነት እና በእኩልነት ለመመለስ በትኩረት ይሰራል።

የሚነሱ የልማትና የመልካም አስተዳደር ስራዎች የሚመለሱት ሰላም ሲኖር በመሆኑ ሁሉም ለሰላሙና ለአንድነቱ በጋራ መስራት እንደሚገባ እና ጽንፈኛ ሀይሎች ለህግ እንዲቀርቡ በጋራ መስራት ያስፈልጋል ነው ያሉት።

ጉራጌ ለዘመናት ከመንግስት ጎን ሆኖ እየሰራቸው ያሉና የሚታወቅባቸው አኩሪ ባህሎቹ አጠናክሮ ማስቀጠል አለበት ያሉት ዶ/ር መሀመድ የወልቂጤ ከተማ ማስተር ፕላን ተግባራዊነት የክልሉ መንግስት በህጋዊ መንገድና በውይይት እንዲፈታ እየሰራ እንደሆነ ገልጸዋል።

በመጨረሻም መድረኩ ባለ 6 የአቋም መግለጫዎችን በማውጣት ተጠናቋል።

መረጃው፦ የጉራጌ ዞን የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን

Previous የመሬት ሊዝ ጨረታ

Leave Your Comment

የቋንቋ አማራጭ

🇺🇸 English
🇪🇹 አማርኛ
🇪🇹 Afan Oromo