ጽህፈት ቤቱ በከተማ አስተዳደሩ ኤዋንና ጩቋራ ቀበሌ ላይ አርሶ አደሩ የተሻሻለ ዝርያ ያላቸውን እንሰሳት እንዲጠቀም ላሞችን በሆርሞን የማድራት ስራ አስጀምሯል።
አቶ አሚር ዲኖ እና አቶ መኪ በድር በኤዋንና ጩቋራ ቀበሌ ላሞቻቸው በሆርሞን በማድራት ላይ ሳሉ አግኝተን ያነጋገርናቸው አርሶ አደሮች ናቸው።
አርሶ አደሮቹ የተሻሻለ ዝርያ ያላቸውን ላሞች ማርባት ሁለንተናዊ ጠቀሜታ እንዳለው ተረድተው ያሏቸውን ላሞች በሲንክሮናይዜሽን ወይም በሆርሞን ለማድራት መምጣታቸውን ገልፀዋል።
ከዚህ ቀደም በባህላዊ መንገድ ላሞችን አርብተው ይጠቀሙ የነበረው የወተትና የስጋ ምርት ውስን እንደነበረም ጠቁመዋል።
ሌሎች አርሶ አደሮችም የተሻሻለ ዝርያ ያላቸውን ላሞችን በማርባት የወተትና የስጋ ምርታቸውን ማሳደግ እንደሚችሉም ተናግረዋል።
አርሶ አደሮቹ አክለውም ከባለሙያዎች የተሰጣቸውን ትምህርት ተቀብለው ተግባራዊ በማድረግ እንደሚሰሩም ጠቁመዋል።
በወልቂጤ ከተማ አስተዳደር ኤዋንና ጩቋራ ቀበሌ ላይ ላሞችን በሆርሞን የማድራት ስራ በተጀመረበት ወቅት የተገኙት የከተማ አስተዳደሩ ከንቲባ አቶ እንዳለ ስጦታው አርሶ አደሩ የተሻሻለ ዝርያ ያላቸው ላሞችን በመጠቀም የወተትና የስጋ ምርቱን ማሳደግ ይኖርበታል ብለዋል።
በዚህም መንግሥት ከፍተኛ በጀት መድቦ አርሶ አደሩ የተሻሻለ የእንስሳት ዝርያ እንዲጠቀም እያደረገ ነው ያሉት ከንቲባው አርሶ አደሩም ይህን በሚገባ መጠቀም ይኖርበታል ሲሉም ገልፀዋል።
በግብርናው ዘርፍ የተሰማሩ አካላት ከራሳቸው አልፎ ለገበያ እንዲያቀርቡ መስራት አለበት በማለት የብልጽግና መንግሥትም ቀጣይነት ያለው ድጋፍ እንደሚያደርግ ጠቁመዋል።
በዋናነት በከተማው ከዚህ ቀደም የነበረውን የወተት ምርት እጥረት እየተሻሻለ መምጣቱን ገልፀው ይህን ለማስቀጠልና በሌሎች ዘርፎች ላይ የሚስተዋሉ ውስንነቶችን ለመቅረፍ በተለይም በሌማት ትሩፋት ላይ ትኩረት ሰጥቶ እንደሚሰራም አቶ እንዳለ ስጦታው ተናግረዋል።
የወልቂጤ ከተማ አስተዳደር ግብርና ጽህፈት ቤት ኃላፊ ዶክተር ወልደማሪያም ዘሬ በበኩላቸው በግብርናው ዘርፍ የከተማው ማህበረሰብ ተጠቃሚ ለማድረግ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑን ገልፀዋል።
በተለይም በከተማው የወተትና የስጋ ምርት ለማሳደግ በዘርፉ ለተሰማሩ አካላት ግንዛቤ ከመፍጠር ጀምሮ የተለያዩ ድጋፍና ክትትል ስራዎች እየተሰራ ስለመሆኑም አንስተዋል።
በዛሬው እለትም በከተማ አስተዳደሩ ኤዋንና ጩቋራ ቀበሌ ላይ አርሶ አደሩ የተሻሻለ ዝርያ ያላቸውን እንሰሳት እንዲጠቀም ላሞችን በሲንክሮናይዜሽን ወይም በሆርሞን የማድራት ስራ መጀመሩን ጠቁመው በቀጣይም በከተማው ስር በሚገኙ ሁሉም ቀበሌዎች ላይ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም አስረድተዋል።
በተያዘው በጀት አመት በከተማ አስተዳደሩ ከ4 መቶ 5O በላይ ከብቶች በሆርሞን ለማድራት ዕቅድ ተይዞ ወደ ተግባር መገባቱን አመላክተዋል።
አሁን ላይ በከተማው የሚገኙ አርሶ አደሮች የተሻሻለ ዝርያ ያላቸውን ላሞች በማርባት የወተት ምርታቸውን አሳድገዋል ያሉት ኃላፊው ይህም ለከተማው የሚቀርበው የወተት ፍጆታ ከፍ እንዲል አድርጎታል ብለዋል።
በመደበኛ በሆርሞንና በኮርማ የእንስሳት ዝርያ ለማሻሻል እንደሚሰራ ተናግረው ማህበረሰቡም በትእግስት ክትትል በማድረግ ዝርያቸውን የማሻሻል ስራ መስራት እንደሚጠበቅበትም መልእክት አስተላልፈዋል።
የጉራጌ ዞን ግብርና መምሪያ ምክትል ኃላፊ አቶ መሐመድ ሙደሲር በዞኑ በሚገኙ ሁሉም መዋቅሮች አርሶ አደሩ የተሻለ የወተትና የስጋ ምርት እንዲያገኝ እየተሰራ ነው ብለዋል።

በዋናነት በወልቂጤ ከተማ አስተዳደር የሚገኙ አርሶ አደሮች የተሻሻለ ዝርያ ያላቸውን እንሰሳት እንዲጠቀሙ በሆርሞን የማድራት ስራ ከተጀመረ ስምንት አመት ያስቆጠረ መሆኑን ጠቅሰው በዚህም ለውጥ የታየ በመሆኑ አሁንም ተጠናክሮ መቀጠሉን ጠቁመዋል።
በተያዘው በጀት አመት በዞኑ ከ22 ሺህ በላይ እንሰሳት በመደበኛ በሆርሞንና በኮርማ ዝርያቸውን ለማሻሻል ዕቅድ ተይዞ ወደ ተግባር መገባቱን ገልፀው ለውጤታማነቱም በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።


Good