
ግንቦት 28/2016 ዓ.ም [ወልቂጤ ]
ለከተሞች መሠረተ ልማት እና በከተሞች ፅዳት ላይ ህዝብና ባለድርሻ አካላትን በማሳተፍ ውጤት ያለው ስራ መስራት እንደሚገባ ተገለፀ ።
“ፅዱ ከተሞች ለኢትዮጵያ ከፍታ ” በሚል መሪ ቃል በከተሞች የፅዳትና አረንጓዴ ልማት ስራዎች ከተማዊ የንቅናቄ መድረክ በጉራጌ ዞን በወልቂጤ ከተማ ተካሄደ ።
ማዕከላዊ ኢትዮጵያዊ ክልል ትራንስፖርት እና መንገድ ልማት ምክትል ቢሮ ሀላፊ እና የመሰረተ ልማት ክላስተር ማስተባበሪ ሀላፊ የሆኑት አቶ አማን ኑረዲን እንደገለፁት የመድረኩ ዋና አላማ እንደ ሀገር የተቀመጠውን አቅጣጫ በመከተል ፅዱ ከተማ መፍጠር ነው ።ከዚህም አንፃር ዜጎች የሚኖሩበትን ግቢ እና አካባቢያቸውን በማፅዳት ፅዱና ማራኪ በማድረግ ለነዋሪዎቿ ምቹ የሆነች ወልቂጤን ለመፍጠር ሁላችንም የድርሻችንን ልንወጣ ይገባል ሲሉ ገልፀዋል ።

በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክላስተር ውስጥ የሚገኙ ከተሞች ሁሉ ከቆሻሻ የፀዱ በማድረግ የአረንጓዴ ልማት ተጠቃሚ እንዲሆኑ በማስቻል ከሌሎች የሀገራችን ከተሞች ተወዳዳሪ የማድረግ ስራዎች ተጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸው አስገንዝበዋል ።
የጉራጌ ማህበረሰብ የማይመጥነውን የቆሻሻ አወጋገድ ስርዓት በማሻሻል እና አረንጓዴ ልማትን በሁሉም አካባቢ በመፍጠር ማህበረሰቡን ሊመጥን የሚችል ስራዎች እየሰራን መስተካከል ያለባቸውን ችግሮች እየፈታን የምንሄድበትን አግባብ እንፈጥራለን ብለዋል።
የትራፊክ ማኔጅመንታችን በመፈተሽ ፣የመንገድ ልማት ትኩረት በመስጠት ፣በከተማዋ መገኘት በማይገባቸው ቦታ የሚታዩ እንስሳት ገደብ ሊበጅለት እንደሚገባ ገልፀው እንዲሁም የውሀ አቅርቦት ለአንድ ከተማ ፅዳት ወሳኝ በመሆኑ በዞኑ ያለውን በቂ የውሀ ሀብት ለመጠቀም የማኔጅመንት አሰራር በመፈተሽ ህገወጥ ቅጥያዎችን የመከታተልና የቁጥጥር ስራዎች ተጠናክረው ሊሰራባቸው እንደሚገባም አብራርተዋል ።

የጉራጌ ዞን ኢንቨስትመንት መምሪያ ሀላፊ አቶ ናስር ሀሰን እንደተናገሩት የጉራጌ ዞን ዋና መቀመጫና የበርካታ የክልል ቢሮዎች መቀመጫ የሆነችውን ወልቂጤ ከተማን ፅዱና ማራኪ አንዲሁም ለነዋሪዎቿ ምቹ የሆነች ከተማን ለመፍጠር መረባረብ ይኖርብናል ብለዋል።
አያይዘውም እንደ ዞን የቆሻሻ አወጋገድ ስርዓታችን ጥሩ ባለመሆኑ በህብረተሰቡ ጤና ላይ ከፍተኛ ጉዳት እያደረሰ እንደሚገኝ ገልፀዋል ።

አቶ ናስር ሀሰን አክለውም በከተማችን የአረንጓዴ ልማትን ለማፍጠንና የቆሻሻ አወጋገድ ስርዓታችንን የሚስተዋለው ከፍተኛ የግንዛቤ ችግር በመሆኑ ይህን ለመቅረፍ የከተማውን ማህበረሰብ እንዲሁም ወጣቱን በማሳተፍና በማቀናጀት ወልቂጤን ከተማን ፅዱና ማራኪ ለማድረግ ነዋሪው በባለቤትነት እንዲቀሳቀስ የማስቻል ስራ ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።

የወልቂጤ ከተማ አስተዳደር ዋና የመንግስት ተጠሪ አቶ አብድልበር ሰኢድ እንደተናገሩት “ፅዳት ለሁሉም ሁሉም ለፅዳት ” የሚለውን መርህ በመከተል በአረንጓዴ ልማትና የፅዳት ስራ ላይ የምናገኘውን ድጋፍና ክትትል በአግባቡ ተጠቅመን ወልቂጤን ከተማን የተሻለች ለነዋሪዎቿ ምቹ እንድትሆን የተጀመሩ ስራዎችን በጋራ በመሆንና ህብረተሰቡን በማሳተፍ ልንሰራ ይገባል ብለዋል።
ብልፅግና ፓርቲ ትኩረት ሰጥቶ ከሚሰራባቸው ግንባር ቀደም ተግባራት አንዱ የፅዳትና የአረንጓዴ ልማት ስራ በመሆኑ ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል በማሳተፍ ከትውልድ ወደ ትውልድ የሚሸጋገር ስራን በመስራት በሁሉም ዘርፍ የተሻለችና ተምሳሌት የሆነች ወልቂጤ መፍጠር ከሁላችንም ይጠበቃል ሲሉ ተናግረዋል።

በውይይት መድረኩ የተገኙት የወልቂጤ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ተወካይ እና የአስተዳደር ፅህፈት ቤት ሀላፊ የሆኑት አቶ ግርማ ንቅበሸዋ እንደገለፁት አካባቢዎችንን ፅዱ ለማድረግ የተጀመረው አቅጣጫ በመከተል ከተማችንን ለነዋሪዎቿ ምቹ እንድትሆን ህዝቡን በማሳተፍ ልንሰራ ይገባል ብለዋል።
አያይዘውም እንዲሁም ለአረንጓዴ ልማት መሳካት የሁሉም ርብርብ እና ትኩረት አስፈላጊ በመሆኑ ሁላችንም ተሳታፊ በመሆን ከተማችንን በአረንጓዴ ልማቱ ዘርፍ የተሻለች እንድትሆን ማድረግ ይጠበቅብናል ሲሉ ተናግረዋል ።

የወልቂጤ ከተማ ማዘጋጃ ቤታዊ አገልግሎት ፅህፈት ቤት ሀላፊ አቶ ይብጌታ ንጋ የከተማችን ነዋሪዎች ግቢያቸውንና አካባቢያቸውን መሰረት ያደረገ ፅዳት በማድረግ እና ለአረንጓዴ ልማት የተለዩ ቦታዎችን በማልማት ዘላቂነት ባለው መልኩ ህብረተሰቡ ባለቤት እንዲሆን የማድረግ ስራዎችን ላይ በቅንጅት መስራት ይገባል ብለዋል።
የከተማችንን ፅዳት ለመጠበቅ የወጡ አዋጆችን ተግባራዊ ለማድረግ የከተማዋ ነዋሪ አጋዥ በመሆን እንዲሁም የከተማችን አረንጓዴ መሰረተ ልማቶች የአካባቢው ህብረተሰብ ፍላጎት መተዳደር እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።
በንቅናቄ መድረኩ ከተሳታፊዎች ከተነሱ ሀሳብና አስተያየቶች መካከል ከቆሻሻ አወጋገድ ስርዓት የግንዛቤ ችግሮች በመኖራቸው አሁንም ፈጥነን ወደ ተግባር በመግባት በግንዛቤ ስራ ላይ ትኩረት ተሰጥቶ ሊሰራ እንደሚገባም አንስተዋል።

አሁን ያለው የፅዳት ስርዓት ወልቂጤ ከተማን የማይመጥን በመሆኑ አሁን የተጀመረውን የአረንጓዴ እና የፅዳት ዘመቻ (ንቅናቄ ) የከተማችንን መልካም ገፅታን ለመገንባት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚኖረውም አንስተዋል ።
እንዲሁም ሁሉም በባለቤትነት ከቤቱ ጀምሮ አካባቢውን በፅዳትና በአረንጓዴ ልማት ስራ ላይ በመሳተፍና ተወዳዳሪ በመሆን በውጤት ስራዎችን እያየን መሄድ መቻል አለብን ብለዋል።
በመጨረሻም በውይይት መድረኩ የተገኙ አካላት ለወልቂጤ ከተማ ለፅዳትና ለአረንጓዴ ልማት ስራ በቅንጅት ለመስራት ቃል የገቡ ሲሆን እንዲሁም የግልና የመንግስት ተቋማት እና በከተማው የሚገኙ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት በከተማዋ በተመረጡ ቦታዎች ላይ በተለያዩ በልማት ስራዎች በመሳተፍ ለማልማት የክብር ፊርማቸውን አኑረዋል።

