
የካቲት 21/2018ዓ.ም [ወልቂጤ ]
በጉራጌ ዞን ወልቂጤ ከተማ ዓድዋ አደራ አንድነት ፣ሉዓላዊነት እና ማንሰራራት” በሚል መሪ ቃል የወጣቶች የውይይት መድረክ ተካሄደ።
በውይይት መድረኩ የወልቂጤ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ሙራድ ከድር እንደገለፁት የዓድዋ ድል በዓል ስናከበር ድሉ ከትላንቱ የዓድዋ ጦርነት ባሻገር ለዛሬው ሀገራዊ ግንባታና ለነገው የብሔራዊ ከፍታ እንደ መነሻ ሊያገለግለንና ልንጠቀምበት ይገባል ብለዋል።
ዓድዋ ድል በዓል አባቶቻችን ካስከበሩት የፖለቲካ ነፃነት ተነስተን የዛሬው ትውልድ የስራ ባህሉን እያሳደገ፤ የፈጠራ አቅሙን እያጎለበተ የኢኮኖሚ ነፃነቱን ተጠቅሞ ሀገራዊ ብልፅግናን ማረጋገጥ የሚያስችል የአስተሳሰብ አንድነት መፍጠር ይኖርበታል ሲሉ ተናግረዋል።
የከተሞች ሁለንተናዊ ልማትና እድገት ለማረጋገጥ እንደሀገር የተጀመሩ የተለያዩ ኢኒሼቲቭ ስራዎች በተለያዩ አካባቢዎች ተግባራዊ በማድረግ በህዝብ ተሳትፎ ከተማችንም ግንባር ቀደም ተጠቃሚ ከተማ ሆናለች።

ሀገራዊ ብልፅግናን ማረጋገጥ የዘመኑ ዓድዋ ነው ያሉት ከንቲባው በጀመርነው ፍጥነት እና የተፈጠረውን የተደመረ ሀገራዊ አቅም ተጠቅመን ድህነትን ድል በማድረግ ተወዳዳሪ የሆነ ጠንካራ የኢኮኖሚ መሠረት ያላት ሀገር መገንባት ይገባል ብለዋል።
ወደ ብልፅግና ማማ ለመድረስ የምናደርገው ጉዞ እንደ ዓድዋ ጦርነት ሁሉ ነገን አሻግሮ የሚመለከት ራዕይ፤ ከፍተኛ መስዋዕትነት፣ ጥረትንና ፅናትን የሚጠይቅ አድካሚና ውስብስብ ጉዞ ቢሆንም እንደ ዓድዋ ጀግኖች በፈተና ውስጥ እየተሻገርን የኢኮኖሚ ድል ማስመዝገባችን የማይቀር በመሆኑ ወጣቱ በባለቤትነት ሊያግዝ እና የከተማችን ሁለንተናዊ ብልፅግና ልናረጋግጥ ይገባል ሲሉ ጠቁመዋል።
ከተማዋ እየተሰሩ ያሉ የልማት ስራዎች የጥራት ጉዳይ ላይ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑን ያነሱት ከንቲባው በተለይ የገጠር ቀበሌዎቻችን ከመሰረተ ልማት ዝርጋታ ጋር ተያይዞ የሚነሱ ጥያቄዎች ለመፍታት ጥረቶች ተጠናክረው ይቀጥላሉ ብለዋል ።እንዲሁም ለዚህም ህዝቡም ተሳትፎ አጠናክሮ መቀጠል እንዳለበትም መክረዋል።
ቀጣይ በከተማችን የምናከናውናቸው የልማት ስራዎች መካከል 2ኛ ዙር የኮሪደር ፕሮጀክት ፣የመሶቦ አገልግሎት ስራዎች ለማስጀመር የቅድመ ዝግጅት ስራዎች መጠናቀቃቸውን ተናግረዋል።

የወልቂጤ ከተማ አስተዳደር ዋና የመንግስት ተጠሪ አቶ ታደለ በቀለ እንደተናገሩት ዓድዋ ስናስብ ከነጠላ ትርክት ወጥተን የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚና የማህበራዊ ጫና ነፃ ሆነን
በሀገራዊ አንድነት ላይ አዲስ እይታና አስተሳሰብ የጥቁር ህዝቦች የነፃነት ድል በመሆኑ በጋራ በመቆም በዓድዋ እሴቶችን ልንጠቀም ይገባል ብለዋል።

የመደመር ፍልስፍና እንደሚያስተምረን፤ የዓድዋን ድል ያለፉትን ስኬቶች በመጠበቅ፣ የታሪክ ስብራትን በመጠገን እና በአዲስ የፈጠራ ስልት ወደፊት በመዝለል፣ የኢትዮጵያን ትንሳኤ በጋራ እሴት ላይ መቆም እንደሚገባ ተናግረዋል።

በአንድነትና ህብረ ብሔራዊነነት በማጠናከር ብልፅግና ፓርቲ በሁሉም ዘርፍ ውጤት በማስመዝገብ ሰርቶ ማሳየቱን አብራርተዋል ።
ዓድዋ ድል ኢትዮጵያ ለጀመረችው የብልፅግና ጉዞ የሚኖረውን ፋይዳ ሀገራዊ ብልፅግናን ያለ እንቅፋት በማስቀጠል ወዳስቀመጥነው ግብ በጥቂት ዓመታት ውስጥ ለመድረስና ርዕያችንን አውን ለማድረግ ልክ እንደ ዓድዋ ጠንካራ ውስጣዊ አንድነት እና በፈተናዎች የማይበገር ትውልድ መሆን እንዳለበትም መክረዋል ።

አባቶቻችን ያስረከቡን ሀገር ሉዓላዊነቷን ጠብቀን እና የምግብ ዋስትናችን አረጋግጠን፣ ስራ ፈጠሪና ከጠባቂነት የወጣ ትውልድ በመውጣት አለም የደረሰበት ቴክኖሎጂ ጋር እኩል እንዲራመድ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ ሲሆን ሁሉም በባለቤትነት አጋዥ ሊሆን እንደሚገባም አንስተዋል ።
በውይይት መድረኩ የተሳተፉ የተገኙ ወጣቶች በሰጡት አስተያየት አድዋ ድል የሁላችንም የኢትዮጵያን የጋራ ታሪክ በመሆኑ ለሀገራች ሉዓላዊነቷ ሊከበር እና ጠንካራ ሀገራዊ ህገመንግስታዊ መፍጠር እንደሚገባ ተናግረዋል ።
ብልፅግና ፓርቲ የጀመራቸውን ሀገራዊ ልማትና እድገት ለማስቀጠል ወጣቱ የበኩሉን ሊወጣ እንደሚገባ ገልፀዋል።

በከተማዋ ህዝቧ የሚመጥን ያላትን ሀብት በአግባቡ ጥቅም ላይ በማዋል የሚገኙ እድሎች መጠቀም ይገባል ብለዋል።
የከተማው ዘላቂነት ያለው ሰላም ለማስፈን መንግስትና ፓርቲ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል ያሉት ወጣቶቹ በሁሉም ዘርፍ ለከተማዋ ልማትና እድገት የበኩላቸውን እንደሚወጡ ተናግረዋል።

በውይይት መድረኩ 7ኛው ሀገራዊ ምርጫ ሠላማዊ ፣ዴሞክራሲያዊ፣ታዓማኒና ቅቡልናት ያለው ሆኖ እንዲጠናቀቅ የወጣቶች ድርሻ ከፍተኛ በመሆኑ የበኩላቸውን መወጣት እንዳለባቸው ተጠቁሟል።
በመጨረሻም በውይይት መድረኩ በተሳታፊዎች ለተነሱ ሀሳቦች ከመድረኩ ሰፊ ማብራሪያና ምላሽ ተሰጥቶ መድረኩ ተጠናቋል።

