የካቲት 16/2018 (ወልቂጤ) በጉራጌ ዞን በወልቂጤ ከተማ ለሚገነባው መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ፕሮጀክት ዱዛይን ላይ የክልሉ፣ የዞንና የወልቂጤ ከተማ የቴክኒክ ኮሚቴ አባላት የውይይት መድረክ አካሄዱ።

የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ፐብሊክ ሰርቪስና የሰው ሀብት ቢሮ ምክትል ኃላፊ ወ/ሮ አስቴር ይርዳው መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት የመንግስት አገልግሎትን በከፍተኛ ሁኔታ የሚያቀላጥፍ መሆኑን ገልፀዋል፡፡
መንግስት ለሰው ተኮር አገልግሎት የሰጠው ትኩረት የተግባር ማረጋገጫ ማዕከል እንደሆነ የጠቀሱት ኃላፊዋ ፤ ህብረተሰቡ ባልተንዛዛ ቢሮክራሲ እንዲሁም በተቀላጠፈ መንገድ አገልግሎት እንዲያገኝ ለማስቻል የተጀመረ ኢንቬቲቭ እንደሆነ አስረድተዋል።
በመሆኑም በማዕከላዊ ክልል በ17 ከተሞች መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ለማስጀመር የቅድመ ዝግጅት ስራዎች እየተከናወኑ መሆናቸው ወ/ሮ አስተለር አስገንዝበዋል።

የጉራጌ ዞን ፐብሊክ ሰርቪስ እና የሰው ሀብት ልማት መምሪያ አቶ ጥላሁን ሽምነሳ ህብረተሰቡ የሚፈልገውን አገልግሎት በጥራት በማቅረብ ከዚህ ቀደም ይስተዋሉ የነበሩ የአገልግሎት አሰጣጥ ጥራትና የመልካም አስተዳደር ችግሮች ያስቀራል ብለዋል።
ማዕከሉ የተቀናጀ አገልግሎት ለተገልጋዩ መስጠት የሚያስችል ትልቅ ውጤታማ ስራ መሆኑንም ገልጸው፤ ማዕከሉን በማደራጀት ወደ ስራ መገባቱ በሀገሪቱ የታለመውን ለውጥ ለማምጣት ወሳኝ ነው ብለዋል፡፡

ማዕከሉ ቅሬታ ይቀርብባቸው የነበሩ አገልግሎቶችን ወደ ዲጂታል በማስገባት የተቀላጠፈ አገልግሎት መስጠት የሚያስችል ትልቅ እርምጃ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡
በኢትዮጵያ የዲጂታል ኢኮኖሚ ሽግግር ትልቅ እርምጃ መሆኑን ጠቅሰው፤ ለብዙ ግዜ በመንግስት ተቋማት የነበሩ የአገልግሎት አሰጣጥ ችግሮችን እንደሚፈታ ተናግረዋል።

የወልቂጤ ከተማ ከንቲባ አቶ ሙራድ ከድር ፕሮጀክቱ በአገልግሎት አሰጣጥ ሂደት የሚስተዋሉ የአገልግሎት አሰጣጥ ጥራት ጉድለትና የመልካም አስተዳደር ችግሮች ለመቅረፍ ፕሮጀከወቱ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያበረክታል ብለዋል።
ከተማው ወደ ስማርት ሲቲነት ለመቀየር በርካታ ተግባራት እየተከናወኑ መሆናቸውን የገለፁት ከንቲባው የተጀመሩ ስራዎች ይበልጥ ውጤታማ ለማድረግ ፕሮጀክቱ አጋዥ እንደሆነ አስገንዝበዋል።

በመሆኑም በፕሮጀክቱ ዲዛይን ላይ ማስተከከያ እንዲደረግባቸው አስተያየት የተሰጠባቸው ተግባራት በማስተካከል ደረጃን በጠበቀ እና ወጪ ቆጣቢ በሆነ መንገድ መሰራት እንዳለበት ተናግረዋል።

ማዕከሉ እስከ 30 የሚሆኑ ካውንተሮች፣ የእንግዳ የመቀበያ ክፍል (Reception)፣ የእረፍት፣ የጥበቃ እና ካፌቴሪያ ክፍል (Relaxation & Waiting with Cafeteria)፣ የህፃናት ማቆያ (Day Care)፣ የመረጃ ማዕከል (Data Center)፣ መዝገብ ቤት እና መጋዘን (Archive & Store)፣ የበጎ ፈቃደኞች ጠረጴዛ (Volunteer Desk)፣ የአስተዳደር ቢሮዎች (Administration Offices)፣ የስልጠና ክፍሎች (Training Rooms)፣ የአስተባባሪ እና የቅሬታ ሰሚ ቢሮዎች (Coordinator & Compliant Offices እንዳሉት ገልፀዋል።

የቴክኒክ ኮሚቴ አባላት ከስታንዳርድ፣ ከጥራትና ከዋጋ ጋር በርካታ አስተያየቶች የሰጡ ሲሆን ከሻጊ የግንባታና ዲዛይን የስራ ኃላፊዎች ማብራሪያ ተሰጥቶባቸዋል ሲል የጉራጌ ዞን ኮሙዩኒኬሽን ዘግቦታል

