ከድህነት የተላቀቀ ማህበረሰብ ለመፍጠር የተጀመሩ የተቀናጀ የግብርና ልማት ስራዎች አጠናክሮ ማስቀጠል እንደሚገባ የጉራጌ ዞን አስተዳደር አስታወቀ።
ጥር 15/2018(ወልቂጤ)
የጉራጌ ዞን ግብርና መምሪያ የ2018 ዓ.ም የበልግ ወቅት የተቀናጀ የግብርና ልማት ስራ የንቅናቄ መድረክ በወልቂጤ ከተማ አካሂዷል።

የጉራጌ ዞን ዋና የመንግስት ተጠሪ አቶ አለማየሁ ገ/መስቀል እንዳሉት ከዚህ በፊት በዞኑ በተሰሩ የተፋሰስ ልማት ስራዎች የግብርና ምርታማነትን እንዲጨምር ከማድረጉ ባለፈ የአካባቢውን ስነምህዳር እንዲቀየር አድርገዋል።
የተፋሰስ ልማት ስራ ከግል ማሳ፣ካልታረሱ መሬቶችና ከባህር ዛፍ ማንሳት ጋር በማስተሳሰር የላቀ ስራ ማከናወን ይገባል ብለዋል።
አቶ አለማየሁ አክለውም እንደ ሀገር በቦቆሎና በወተት ምርታማነት የተገኘው ሞዴል ተግባር በማሳደግና በሌሎች በሁሉም ዘርፎች እየተከናወኑ ያሉ ተግባራት ወደ ውጤት መቀየር እንደሚገባ አስታውቀዋል።
የማህበረሰባችን ንቃተ ህሊናና የልማት ተነሳሽነት እንደምቹ አጋጣሚ በመጠቀም ለህዝቡ ዘላቂ ጥቅም ላይ ያተኮረ የልማት ስራ እንዲሰራ አብራርተዋል።

የጉራጌ ዞን ምክትል አስተዳዳሪና የግብርና መምሪያ ኃላፊ አቶ አበራ ወንድሙ እንደገለፁት የተቀናጀ የግብርና ልማት ስራዎች ይበልጥ በማጠናከር ከድህነት የተላቀቀ ማህበረሰብ መፍጠር ያስፈልጋል።
በዞኑ በሌማት ትሩፋት የተጀመሩ ስራዎች ይበልጥ ማሳደግ ይጠይቃል ያሉት አቶ አበራ በቡና፣በእንስሳት፣በተፈጥሮ ሀብት፣በእርሻ፣በመሬት አጠባበቅና በሌሎችም ላይ በትኩረት እንዲሰራ አስገንዝበዋል።
አቶ አበራ አክለውም የሀይማኖት፣የመንግስትና የአርሶ አደር መሬቶች ሁሉም እንዲታረስ አጽንኦት የሰጡ ሲሆን የግብርና ግብአቶች በአግባቡ ማሟላትና በግብርና ዘርፉ የሚግጥሙ ችግሮች ለይቶ መቅረፍ እንደሚገባ ገልጸዋል።
ከተረጂነት ወደ ምርታማነት ለመሸጋገር የሚደረጉ ተግባራቶች አበረታች ቢሆኑም በቂ ቅድመ ዝግጅት ማድረግና አስቀድሞ መከላከል ላይ አትኩሮ መስራት ያስፈልጋል ነው ያሉት።

በዘንድሮ አመት 88 ሺ 5መቶ 81 ሄክታር መሬት በተፋሰስ ልማት ለማልማት በቂ ቅድመ ዝግጅት ተደርጓል ሲሉ አቶ አበራ አስታውቀዋል።
የጉራጌ ዞን ምክር ቤት የኢኮኖሚ ዘርፍ ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ወ/ሮ ጠጄ ደነቀ በጉራጌ ዞን በግብርና ዘርፍ ውጤታማ ስራዎች እየተሰሩ ይገኛል።
ከተረጂነት ወደ ምርታማነት ለመሸጋገር የተሰሩ ስራዎች አበረታ ቢሆኑም በአግባቡ ተደራሽ ከማድረግ አንጻር የበለጠ መስራት እንደሚያስፈልግ አመላክቷል።
ግብርናው ይበልጥ ለማሳደግ የግብርና ጣበያ ሰራተኞች አርሶ አደሩን በአግባቡ ማገልገል ይጠበቅባቸዋል ብለው ለባለሙያውና ለአርሶ አደሩ በቂ ስልጠናዎች እንዲሰጥ ወ/ሮ ጠጄ አንስተዋል።

የጌታ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ በህሩ ኸይረዲንና የእዣ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ዘውዱ ዱላ እንዳሉት በወረዳቸው አበረታች የተቀናጀ የግብርና ስራዎች በመስራት የአርሶ አደሩን ኑሮ ከጊዜ ወደ ጊዜ ማሻሻል ተችሏል።
ግብርናው ለስራ እድል ፈጠራ፣ለምግብ ዋስትና፣የውጭ ምርቶች ለመተካት፣የኢንድስትሪ ግብአቶች ለማቅረብና በአጠቃላይ ከድህነት ለመውጣት የአንበሳውን ድርሻ ይወስዳል ብለዋል።

በተፋሰስ ጉዳይ የአርሶ አደሩን ግንዛቤ አድጓል ያሉት ሀሳብ ሰጪዎች አርሶ አደሮች ተፋሰስ “የመሬት ሀኪም ነው” ብለው እየሰሩበት ይገኛል ሲሉ ገልጸዋል።

