የጤና ባለሙያዎች ጥያቄ የአፍራሽ ሀይል መጠቀሚያ እንዳይሆን የዞኑ ጤና ባለሙያዎች በመደበኛ ስራቸው ላይ ሆነው መወያየታቸው ለህዝባቸው ያላቸውን ውግንና የሚያሳይ መሆኑን የገለጹት አቶ ላጫ ለዚህም አመስግነዋል።
ግንቦት 14/2017ዓ.ም(ወልቂጤ)
======================

በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ጉራጌ ዞን “የጤና ዘርፍ አርበኝነት ለሀገር እድገት” በሚል መሪ ቃል ዞናዊ የጤና ባለሙያዎች ውይይት በወልቂጤ ከተማ ተካሂዷል።
የጉራጌ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ላጫ ጋሩማ እንዳሉት እንደ ሀገር ብሎም እንደ ዞን በባለፋት አመታት መንግስት የጤና አገልግሎት ተደራሽነትና ጥራትን ለማሳደግ በተሰራው ስራ ተጨባጭ ለውጥ ተመዝግቧል።
በጤናው ዘርፍ የሚስተዋሉ ችግሮችን መንግስት ደረጃ በደረጃ ለመፍታት በቁርጠኝነት እንደሚሰራ ገልጸዋል።
የጤና ባለሙያዎች ጥያቄ የአፍራሽ ሀይል መጠቀሚያ እንዳይሆን የዞኑ ጤና ባለሙያዎች በመደበኛ ስራቸው ላይ ሆነው መወያየታቸው ለህዝባቸው ያላቸውን ውግንና የሚያሳይ መሆኑን የገለጹት አቶ ላጫ ለዚህም አመስግነዋል።

የጉራጌ ዞን የመንግስት ዋና ተጠሪ አቶ አለማየሁ ገብረመስቀል በዞኑ በጤናው ዘርፍ በተሰሩ ስራዎች ውጤታማ ስራ መሰራቱን ጠቁመው ለዚህም የጤና ባለሙያዎች ያደረጉት አስተዋጽኦ አመስግነዋል።
መንግስት የጤና ባለሙያዎች እየጠየቁት ያለው ጥያቄዎችን ደረጃ በደረጃ ለመፍታት እንደሚሰራ ገልጸዋል።
የክልሉ ጤና ቢሮ ምክትል ኃላፊና የህብረተሰብ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር አቶ ማሙሽ ሁሴን የጤና ባለሙያዎች የሚያነሷቸው ጥያቄዎችን ለመፍታት ከፌደራል ጀምሮ መንግስት በትኩረት እየሰራ ይገኛል።
በክልሉ የጤና አገልግሎት ተደራሽነትና ፍትሃዊነት ለማረጋገጥ እየተሰራ መሆኑንም ጠቁመዋል።

የጉራጌ ዞን ጤና መምሪያ ኃላፊ አቶ አየለ ፈቀደ በበኩላቸው የመድረኩ አላማ የጤና ባለሙያዎችና ሰራተኞች ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን ጠንካራ የጤና ስርአት ለመገንባትና በሀገር ግንባታ ላይ ሚናቸውን በአግባቡ እንዲወጡ ለማስቻል ነው ብለዋል።

በባለፉት አመታት በጤና ዘርፍ ባለሙያዎች በሰሩት ስራ በርካታ ለውጦች የተመዘገበ መሆኑን ያነሱት ኃላፊው ለዚህም የዜጎች ጤና የመጠበቅ፣ ጤና የማበልጸግ፣ በሽታ የመከላከል፣ አክሞ የማዳንና የታህሶ አገልግሎት በመስጠት ከፍተኛ ስራዎች መሰራቱን ገልጸዋል።
በጤና ዘርፍ የእናቶችና ህጻናት ሞት ለመቀነስ በተሰራው ስራ በርካታ ለውጦች መመዝገቡን ጠቁመው ከዚህም ባለፈ ተላላፊ በሽታዎችንም መከላከልና መቆጣጠር ተችሏል ብለዋል።
የተመዘገቡ ስኬቶችን ለማጠናከርና ጉድለቶችን ለማረም እንዲሁም በጤናው ዘርፍ የተጀመረውን ስራ ውጤታማ ለማድረግ ከባለድርሻ አካላት ይበልጥ በቅንጅት መስራት ይገባል ብለዋል።

የመድረኩ ተሳታፊዎች እንዳሉት የጤና ባለሙያዉ በሀገር ደረጃ የተቀረጸዉን አዲሱን የጤና ልማት ፖሊሲ ለመተግበር በሚደረገዉ ጥረት የራሱን አስተዋጾ ለማበርከት ቃል በመግባት ዉይይቱ ተጠናቋል።
#መረጃው:-የጉራጌ ዞን የመንግሥት ኮሚዩኒኬሽን ነው

