ጤና ጣቢያዎች የውስጥ አሰራራቸው በማዘመን ጥራቱን የጠበቀና ቀልጣፋ የሆነ የጤና አገልግሎት ለመስጠት እየሰሩ እንደሚገኙ የወልቂጤ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ሙራድ ከድር ገለጹ።
ጥር 20/2018ዓ.ም /ወልቂጤ/

በጉራጌ ዞን በወልቂጤ ከተማ አስተዳደር ጤና ጽህፈት ቤት የ3ቱም ጤና ጣቢያዎች የ2018 ዓ.ም የ2ተኛ ሩብ ዓመት የቦርድ አባላት ውይይት ተካሄደ።
ከውይይቱ ቀደም ብሎ የቦርድ አባላቱ የ3ቱም ጤና ጣቢያ የአሰራር ስርዓት፣ እንዲሁም አገልግሎት የሚሰጥባቸው ክፍሎችን አጠቃላይ ገፅታው፣ የእናቶች ክፍል፣ የላብራቶሪ ክፍል የኬሚስትሪ ማሽን ተገዝቶ አገልገሎት እየሰጠ ያለበት ሁኔታ ተዟዙረው የጎበኙ ሲሆን ጤና ጣቢያዎቹ ለደንበኛ ተስማሚ መሆናቸውና በህብረተሰቡ ዘንድ ይነሱ የነበሩ ቅሬታዎች መቅረፍ መቻሉን በጉብኝት ወቅት ተመልክተዋል።

በ3ቱም ጤና ጣቢያ ከኬሚስትሪ ማሽን በተጨማሪ የCBC ማሽን ችግር በአጭር ጊዜ በመቅረፍ ማህበረሰቡ የትም ሳይሄድ በጤና ጣቢያው ሙሉ አገልግሎት ማግኘት እንዲችል የተደረገበት አግባብ መኖሩ ተገልጿል።
መድረኩም በ3ቱም ጤና ጣቢያዎች በ2018 በጀት ዓመት የ2ኛ ሩብ ዓመት የተከናወኑ ተግባራት ዝርዝር ሪፖርት በየጤና ጣቢያ ኃላፊዎች እንዲቀርብ ተደርጓል፡፡

የወልቂጤ ከተማ አስተዳደር ከንቲባና የቦርዱ ሰብሳቢ አቶ ሙራድ ከድር እንዳሉት በወልቂጤ ከተማ አስተዳደር የሚገኙ ጤና ጣበያዎች በአገልግሎት አሰጣጥም ሆነ በውስጥ አደረጃጀት እየተሻሻሉ የመጡ ተቋማት መሆናቸው በምልከታ ወቅት የገለጹ ሲሆን፦
በመጀመሪያው ሩብ አመት በማህበረሰብና በቦርድ ውይይት ወቅት የተነሱ የተለያዩ ጥያቄዎችን በተግባር የተደገፈ ምላሽ ለመስጠት የተሄደበት ርቀትም አበረታች ነውም ብለዋል፡፡

አቶ ሙራድ አክለውም በጤና ተቋም የአገልግሎት አሰጣጥ፣ተላላፊና ተላላፊ ባልሆኑ በሽታዎች ዙሪያ ፣በእናቶችና ህፃናት አካባቢ ክትትሉ ምን ይመስላል በሚሉት ሀሳቦች ዙሪያ በትኩረት ሊሰራባቸው እንደሚገባ አመላክተው
ጤናማ የሆነ የአገልግሎት አሰጣጣችን ልናጠነክረውና ለማህበረሰባችን ስንሰጠው ከነበረው አገልግሎት የበለጠና የተሻለ ሆኖ በማገልገል የማህበረሰባችን የመንፈስ እርካታ ማየት ይኖርብናል ብለዋል።

የወልቂጤ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባና የጤና ጽህፈት ቤት ሀላፊ አቶ ሙባረክ ዘይኑ በበኩላቸው ጤና
ጣቢያዎቹ ከጊዜ ወደ ጊዜ በአሰራርና አገልግሎት አሰጣጣቸውን እያሳደጉ የመጡበትን መንገድ አድንቀው
አጠናክሮ ማስቀጠል እንደሚገባም ተናግረዋል፡፡
ጤና ጣበያዎች አሁን ላይ ያሉበት ደረጃ ጥሩ መሆኑን ጠቁመው በቀጣይ በጤና ጣበያ የሚሰጡ የአገልግሎት አድማስን በማስፋት ወደ ሌላ ቦታ የሚደረጉ ሪፈር ቁጥርን መቀነስ እንደሚቻልም ጠቁመዋል፡፡

የከተማው መንግስትም የጤና ጣቢያ አገልግሎት አሰጣጥ ለማሳደግ በሚደረገው ጥረት ለሚያደርገው ያልተቋረጠ ድጋፍ አመስግነው በቀጣይም በ3ቱም ጤና ጣበያ የባዮ ሜዲካል ባለሙያ አፈላልጎ እንዲቀጥርላቸው አቶ ሙባረክ አሳስበዋል፡፡
አንዳንድ የቦርዱ አባላት በሰጡት አስተያየት የህጻናትና የአዋቂ ተኝቶ መታከሚያ ክፍሎች አለመለየት፣ከቦታ ጥበት አንጻር ተደራቢ ህክምና መስጠት፣የእናቶች ማረፊያ፣የገጠር ቀበሌ ሆነው ጤና ኬላ የሌላቸው አካባቢዎች፣ ከሰራተኛ ጥቅማጥቅምና በርካታ የመልካም አስተዳደር ችግሮች ተነስተው ሰፊ ማብራሪያ ከመድረኩ ተሰጥቶበታል።

የጤና ተቋማት የግብአት፣ የተለያዩ ማሽኖችና የመዳኒት ችግሮች በዘላቂነት ለመፍታትና የጤና ጣበያ የፋይናንስ አቅም ለማሳደግ ከአካባቢው ባለሃብትና ግብረሰናይ ድርጅቶች ፕሮጀክት ቀርጾ በማስተሳሰር ተቋሙን ማሻገር እንደሚቻልም ተመላክቷል ።

