በግማሽ አመቱ ከ3 ቢሊየን 663 ሚሊየን ብር በላይ ወጪ በማድረግ በጀቶች ለታለመላቸው አላማ እንዲውሉ መደረጉ የጉራጌ ዞን ፋይናንስ መምሪያ አስታወቀ።
ጥር 15/2018(ወልቂጤ)

መምሪያው በ2018 በጀት አመት በ6 ወሩ የተሰሩ ስራዎች በተመለከተ ለሚዲያ መግለጫ ሰጥቷል።
የጉራጌ ዞን ፋይናንስ መምሪያ ኃላፊ አቶ አብዶ ሀሰን እንዳሉት ከመንግስት የሚገኘውን በጀት የቀመር መመሪያ መነሻ በማድረግ ፍትሃዊ የሆነ የበጀት ድልድል ይደረጋል።
በዚህም ሴክተር መስሪያ ቤቶችም በፀደቀላቸዉ በጀት መሰረት የደመወዝ፣ የመደበኛ ስራ ማስኬጃና የካፒታል ፕሮጀክቶች ክፍያ፣ጥቅል እና አስቸኳይ ግዢዎችን በመፈጸም የልማት ስራዎች እንዲሰሩ ይደረጋል።
በበጀት አመቱ 7 ቢሊየን 48 ሚሊየን 395 ሺ 502 ብር በዞኑ ምክር ቤት ጸድቆ ወደ ስራ የተገባ ሲሆን ለደሞዝ ለስራ ማስኬጃና ለካፒታል በማከፋፈል ለልማት እንዲውል ሲሰራ እንደነበር አስታውሰዋል።
በግማሽ ዓመቱ ከ3 ቢሊየን 663 ሚሊየን ብር በላይ ወጪ በማድረግ በጀቶች ለታለመላቸው አላማ እንዲውሉ መደረጉ አቶ አብዶ ተናግረዋል።
ለአብነትም ደሞዝ ብቻ 3 ቢሊየን 66 ሚሊየን 11ሺ 684 ብር ሲሆን የበጀቱ 50 ፐርሰንት የሚሸፍን መሆኑን ጠቁመዋል።
ለስራ ማስኬጃ የጸደቀው 1 ነጥብ 5 ቢሊየን ብር መሆኑን የገለጹት አቶ አብዶ በግማሽ ዓመቱ 7 መቶ 7 ሚሊየን ብር ስራ ላይ ማዋል የተቻለ መሆኑና የበጀቱ 19 ፐርሰንት ብቻ እንደሚፈጅ አመላክተዋል።
ይህ የሚያመላክተው ለሌሎች ስራዎች ይበልጥ ትኩረት መሰጠቱ ሲሆን ይህንን ውስን በጀት በአግባቡ በመጠቀም ለታለመለት አላማ እንዲውል ተደርጓል።
አቶ አብዶ አክለውም የዞኑ መንግስት ለካፒታል ፕሮጀክቶች ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ሲሆን ከተመደበው አጠቃላይ በጀት 35 ፐርሰንቱ ለካፒታል ፕሮጀክቶች የተያዘ መሆኑን አስገንዝበዋል።
በዚህም በዓመቱ 2 ነጥብ 4 ቢሊየን ብር ለካፒታል ፕሮጀክቶች የጸደቀ ሲሆን እስካሁን 1ቢሊየን 15 ሚሊየን ብር ለፕሮጀክቶች ክፍያ ተፈጽሟል ነው ያሉት።
ከእነዚህም ለአብነት የጉራጌ ዞን አስተዳደር ህንጻ ግንባታ፣ለጉራጌ ዞን አማርድ አዳሪ ትምህርት ቤት፣የጉራጌ ባህል ማእከል አዳራሽ ከፍተኛ የገንዘብ ክፍያ የተፈጸመላቸው ሲሆኑ ሌሎችም በየደረጃቸው ክፍያ ተደርጎላቸዋል ብለዋል ኃላፊው።
ከተመደበው በጀት ከ10 ሚሊየን ብር በላይ ለቁሳቁስ ግዢና ለጥገና ማዋል መቻሉ የጠቆሙት አቶ አብዶ በ6 ወሩ በ3ቱ ዋና ዋና ዘርፎች 51 ፐርሰንቱ በጀት ወጪ ተደርጎ ተግባር ላይ ውላል ሲሉ ተናግረዋል።
በጉራጌ ዞን ካሉ ተቋሟት 311ዱ ኦዲት በማድረግ 2 ነጥብ 4 ሚሊየን ብር በጉደለት ሲገኝ እስካሁን 1 ነጥብ 9 ሚለየን ብሩ ተመላሽ ተደርጎ ሌሎች በሂደት ላይ መሆናቸው አብራርተዋል።
እንደ አብዶ ገለጻ በዞን ማእከል ከላፕቶብ እስከ መኪና ያሉ ቋሚ ንብረቶች ቆጠራ ተደርገው በዘመናዊ ሁኔታ በአግባቡ እንዲደራጁ ተደርጓል።
በቀጣይ ከአገልግሎት ውጪ የሆኑ ንብረቶች በአግባቡ በማስወገድና ወደ ገቢ የመቀየር ተግባር በትኩረት ይሰራበታል ሲሉ ጠቅሰዋል።
ልማት በመንግስት ብቻ አይሰራም ያሉት አቶ አብዶ የጉራጌ ማህበረሰብ የልማት ተነሳሽነት እሴት በማጠናከር ገንዘብ በማሰባሰብ የልማት ስራዎች እያከናወነ ይገኛል።
ለአብነትም በመንገድና በትምህርት ንቅናቄ ስራዎች ከፍተኛ ገንዘብ በማዋጣት መንግስት ከሚደጉመው በጀት በተጨማሪ በራስ አቅም የልማት ስራዎች መከናወናቸው ከፍተኛ እገዛ አድርጓል ነው ያሉት።
በየ ተቋሟት የተመደበው በጀት ለታለመለት አላማ እንዲውል ሁሉም የበኩሉ እንዲወጣ አቶ አብዶ መልእክት አስተላልፏል።

