በጉራጌ ዞን የአማርድ አዳሪ ትምህርት ቤት ተማሪዎች የገና በአል በተለያዩ ዝግጅቶች እያከበሩ ይገኛል።
ታህሳስ 29/2018 ዓ.ም (ወልቂጤ

የአማርድ አዳሪ ትምህርት ቤት ተማሪዎች የገናን በዓል በልዩ ልዩ ዝግጅቶች በድምቀት እያከበሩ ነው።
በአማርድ አዳሪ ትምህርት ቤት ተገኝተው በአሉን በጋራ ያከበሩት የጉራጌ ዞን ትምህርት መምሪያ ኃላፊ አቶ መብራቴ ወልደማሪያም እንዳሉት ተማሪዎች የዘንድሮውን የገና በዓል የትምህርት ቤቱን ማህበረሰብ፣ መምህራንና ተማሪዎችን ያሳተፉ የተለያዩ ሃይማኖታዊ፣ ባህላዊና ማህበራዊ ዝግጅቶችን በማድረግ በድምቀት እያከበሩ ይገኛሉ።ተማሪዎቹ በዓሉን አስመልክቶ ያዘጋጇቸውን ግጥሞች፣ አጫጭር ድራማዎች እና ሌሎችም ዝግጅቶች በማቅረብ ማዕድ በጋራ በመብላት ዕለቱን በደስታ እያሳለፉት ይገኛሉ ብለዋል።
በአዳሪ ትምህርት ቤቱ ቅጥር ግቢ ውስጥ ተማሪዎች፣ መምህራን እና ሰራተኞች በአንድነት በዓሉ ቤተሰባዊ ፍቅርንና አንድነትን በጠበቀ መልኩ እንዲያሳልፉ አስፈላጊ ዝግጅቶች መደረጉም ጠቁመዋል።

ተማሪዎቹ በእድሜ ገና ህፃናት በመሆናቸው ከቤተሰቦቻቸው ተለይተው በዓል ሲያከብሩ ገና የመጀመሪያ በመሆኑ የብቸኝነት ስሜት እንዳይሰማቸውና በትምህርት ቤቱ ውስጥ የቤተሰብ ፍቅር እንዲያገኙ ከፍተኛ እገዛ እየተደረገ እንደሆነም አመላክተዋል።
የአማርድ አካዳሚ ርዕሰ መምህር አቶ መላኩ ተረዳ በበኩላቸው ተማሪዎች ቤታቸውን እንዳያስታውሱ ለማድረግና በአብሮነት የገናን በአል በተለያዩ ዝግጅቶች እያከበሩት እንደሆነም አስረድተዋል።
በእለቱ የገና ጫወታ በመጫወት ፣የተለያዩ የስነ ፅሁፍ ስራ በማቅረብና ማዕድ በአብሮነት በመቋደስ በአሉን እያከበሩ እንደሆነም ተናግረዋል።
ተማሪዎችም በበኩላቸው በዓሉን ምንም ሳይከፋቸው ከጓደኞቻቸው፣ ከመምህራኖቻቸውና ሌሎችም እንግዶች ጋር ማክበራቸው ደስተኛ መሆናቸውን ገልፀዋል።

ለበአሉም ከሌላ ጊዜ የተለየ ዝግጅት መደገረጉ እና ምንም ሳይከፋቸው ማክበራቸውና ይህም ለትምህርት ያላቸውን መነሳሳት እንደሚጨምርላቸው ተናግረዋል።
በአዳሪ ትምህርት ቤት ቅጥር ግቢ ውስጥ በበዓሉ አከባበር የጉራጌ ዞን ትምህርት መምሪያ ኃላፊ አቶ መብራቴ ወልደማሪያም ፣የጉራጌ ዞን መንግስት ኮሚኒኬሽን ኃላፊ አቶ ሸምሱ አማን ፣መምህራን ፣ የአማርድ አስተዳደር ሰራተኞች ፣ተማሪዎች እየታደሙ ይገኛል።
የጉራጌ ዞን መንግስት ኮሙዩኒኬሽን መምሪያ ነው

