በጉራጌ ዞን በወልቂጤ ከተማ ተፈጥሮ የነበረው አለመግባባት ለመፍታት የፌደራል ፖሊስ፣ የዞኑ ፖሊስ፣ የወልቂጤ ከተማ ፖሊስ፣ የአበሽጌ ወረዳ ፖሊስና የቀቤና ልዩ ወረዳ ፖሊስ ጋር በወልቂጤ ከተማ ውይይት ተደርጓል።

የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል መንግስት የሰላምና ጸጥታ ቢሮ ኃላፊ አቶ ተመስገን ካሳ የውይይቱ አላማ በቅርቡ በወልቂጤ ከተማ የተፈጠረው አለመግባባት ላይ የህግ የበላይነት ለማስፈን የጸጥታ ሀይሉ የሰራቸው ስራዎች በመገምገም የቀጣይ አቅጣጫ ተቀምጧል ብለዋል።

በዚህም የክልሉ አድማ ብተና የፌድራል ፖሊስ፣ የዞኑ ፖሊስ፣ የወልቂጤ ከተማ አስተዳደር ፖሊስ፣ የአበሽጌ ወረዳ ፖሊስና የቀቤና ልዩ ወረዳ ፖሊስ በመቀናጀት የአከባቢውና የከተማው ሰላም ለማስፈን በተቀመጠው አቅጣጫ መሰረት በርካታ ስራዎች መሰራቱንም አመላክተዋል።

ለአብነትም በህገውጥ ድርጊት የተሳተፉ አካላት ለህግ እንዲቀርቡ መደረጉና በማህበረሰቡ መሀከል ዘላቂ ሰላም ለማስፈን በሚደረገው ጥረት እንቅፋት የሚሆኑ ጥቂት አካላት የማረም ስራ እየተሰራ መቆየቱን አስረድተዋል።

እስካሁን የተከናወኑ ስራዎችን አፈጻጸም በመገምገም በቀጣይ በአካባቢው ዘላቂ ሰላም ለማስፈን አቅጣጫ መቀመጡንም ነው ያነሱት።

ህብረተሰቡ በሰላም ወጥቶ እንዲገባ፣ ነጋዴው ንግዱን በነጻነት መነገድ እንዲችል፣ ተማሪዎች ትምህርታቸውን በነጻነት እንዲማሩና በከተማው የሚያልፉ ዜጎች ያለምንም ስጋት መንቀሳቀስ እንዲችሉ መግባባት ላይ መደረሱንም አስገንዝበዋል።

ወልቂጤ ከተማ በርካታ ተሽከርካሪዎች አቋርጠው የሚያልፉባት ከተማ በመሆኗ ተሽከርካሪዎች፣ ዜጎች ምንም አይነት እንግልትና ህገወጥ ድርጊት ሳይፈጸምባቸው በነጻነት እንዲመላለሱ የጸጥታ ሀይሉ የጀመረውን ስራ አጠናክሮ እንዲቀጥል የቀጣይ አቅጣጫ ተቀምጧል ብለዋል።

ከዚህም ጎን ለጎን በአካባቢው ዘላቂ ሰላም ግንባታ ስራ በአካባቢው አስተዳዳሪዎችና አመራሮች ውይይት ተጀምሯል ያሉት አቶ ተመስገን የተጀመረው ውይይት እንዳይሰናከል የጸጥታ ሀይሉ ከአመራሩ ጎን በመሆን በቁርጠኝነት እንዲሰራ መግባባት ተችሏል ብለዋል።

የሰላም ምንጩ ከግለሰብ፣ ከቤተሰብና ከቡድን ይጀምራል ያሉት ኃላፊው ሁሉም የህብረተሰብ ክፍሎች፣ ወጣቶች፣ የከተማው ነዋሪዎች ከጸጥታ ሀይሉ ጎን በመሆን እየተሰራ ያለው የህግ የበላይነት ስራና የዘላቂ ሰላም ግንባታ ስራ ላይ ከጸጥታ ሀይሉና ከመንግስት ጎን በመሆን እንዲያግዙ አሳስበዋል።

ሰላም እንዲደናቀፍ የሚፈልጉ የግጭት ነጋዴዎች በማህበረሰቡና በብሔር ስም የሚነግዱ አካላት አደብ ሊገዙ እንደሚገባ አስጠንቅቀው ከዚህም ባለፈ እነዚህ አካላት ህብረተሰቡ ለጸጥታ ሀይሉ ጥቆማ መስጠት፣ ማጋለጥና መቃወም እንዳለበትም ገልጸዋል ሲል የዘገበው የጉራጌ ዞን የመንግስት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች መምሪያ ነው።

Previous በግብርና ዘርፍ የሚታየውን መልካም እንቅስቃሴ ቀጣይነት እንዲኖረው የማስቻል ስራ በትኩረት እየተሰራ እንደሚገኝ የወልቂጤ ከተማ አስተዳደር ግብርና ፅህፈት ቤት ገለፀ።

Leave Your Comment

የቋንቋ አማራጭ

🇺🇸 English
🇪🇹 አማርኛ
🇪🇹 Afan Oromo