ግንቦት 16/2017 (ወልቂጤ )

==========================

የትምህርት ጥራትን ለማሻሻል የትምህርት ቤቶችን ደረጃ በማሳደግ እና በዘርፉ የሚገጥሙ ችግሮች ለመፍታት እየተሰሩ ያሉ ተግባራት ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ተገለጸ።

በየደረጃው በሚገኙ በተማሪዎች የተሻለ ውጤት እንዲ መዘገብ በትኩረት እየተሰራ መሆኑ ተገለፀ።

በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በጉራጌ ዞን ‘ትውልድ በመምህር ይቀረፃል ሀገር በትምህርት ይበለፅጋል’ በሚል መሪ ቃል ለመምህራን የተዘጋጀ ዞናዊ የማጠቃለያ ውይይት መድረክ በወልቂጤ ከተማ ተካሄዷል።

የጉራጌ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ላጫ ጋሩማ የትምህር ጥራት ለማሻሻል የትምህርት ቤቶችን ደረጃ ማሻሻል፣ የትምህርት ግብዓትና ቁሳቁስ ማሟላት እና ትምህርት ቤቶች ለመማር ማስተማር ስራ ምቹና ማራኪ እንዲሆኑ በትኩረት መስራት ያስፈልጋል ብለዋል።

ለዚህም ባለፉት ሁለት ዓመታት ዘጠኝ መቶ ሚሊዮን ብር የሚጠጋ ሀብት በማሰባሰብ የትምህርት ቤቶች ጥገናና ግንባታ እና የግብዓት የማሟላት ስራ መሰራቱን አቶ ላጫ ተናግረዋል።

በባለፉት ዓመታት የገጠመንን የትምህርት ስብራት ለመጠገን እንደ ሀገር አዲሱ የትምህርት ስርዓት ተቀርፆ ተግባራዊ ከሆነ ጊዜ ጀምሮ በርካታ የሪፎርም ስራዎች በዞኑ በሚገኙ ትምህርት ቤቶች እየተተገበሩ ይገኛል።

መምህራን የኑሮ ውድነቱን እንዲቋቋሙ በየመዋቅሩ የሸማቾች ህብረት ስራ ማህበራትን እና በየአከባቢው የሰንበት ገበያ ማጠናከር ያስፈልጋል ያሉት አቶ ላጫ የመምህራን የመኖሪያ ቤት ግንባታ ቦታ የማመቻቸት ስራ በየመዋቅሩ በዕቅድ ይሰራል ነው ያሉት።

የጉራጌ ዞን ዋና የመንግስት ተጠሪ አቶ አለማየሁ ገብረመስቀል መምህራን ትውልድ የመቅረፅ ሀላፊነታቸውም አጠናክረው ማስቀጠል አለባቸው ብለዋል።

በትምህርት ልማት ዘርፍ የተጀመሩ የሪፎርም ስራዎች ወደ ላቀ ደረጃ እንዲሸጋገር መምህራን ለሙያቸው እየከፈሉ ያሉት ዋጋ በምንም የሚተመን አይደለም ነው ያሉት።

የትምህር ስብራቱን ለመጠገን እየተከናወነ ያለው ሁሉ አቀፍ ንቅናቄ በውጤት እንዲታጀብ ያስፈልጋልም ብለዋል አቶ አለማየሁ።

በዛሬው የውይይት መድረክ የተነሱ የመልካም አሰተዳደር ችግሮች በተደራጀ መልኩ ደረጃ በጀረጃ ከሚመለከተው አካል በመቀናጀት በዕቅድ የሚፈቱ ይሆናል ብለዋል።

የጉራጌ ዞን ትምህርት መምሪያ ኃላፊ አቶ መብራቴ ወ/ማሪያም በበኩላቸው ዞኑ የትምህርት አመራሩና መምህሩ ያጋጠመን የትምህርት ስብራት ፈጥኖ ለማከም እና የቴክኒክና ሙያ ትምህርትን ለማጠናከር በሚደረገው ትግል አዲስ የተቀረፀው የትምህርት ፖሊሲ ወደ መሬት በማውረድ ህዝብ በማሳተፍ ሰፊ ርብርብ እየተደረገ ነው ብለዋል።

ለዚህ ተግባር ስኬት የተጓደሉ የትምህርት ግብዓቶችን በማሟላትና የመምህራን መኖሪያ ቤት በመገንባትና በመጠገን ስራ እየተከናወነ ነው።

በዚህ ሰፊ ትግል የትምህርት አመራሩና መምህራን ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይሉ በቁርጠኝነት የበኩላቸውን ድርሻ እየተወጡ መሆናቸውን ሀላፊው ገልፀዋል።

አቶ መብራቴ አክለውም የትምህርት ስርዓት ለማሻገር የተጀመሩ ስራዎች ከምንም በላይ በራሱና በሀገሩ ክብርና ጥቅም የማይደራደር ትውልድ ለመገንባት እና የመምህርነትን ሙያ ይበልጥ ተከብሮ ተወዳጅ እንዲሆን የሚያደርግ ነው ሲሉ ተናግረዋል።

የመድረኩ ተሳታፊዎች እንዳሉት በትምህርቱ ዘርፍ በሀገር ደረጃ የተቀረጸዉን አዲሱን የስርዓተ ትምህርት ፖሊሲ ለመተግበር በሚደረገዉ ጥረት የራሳቸውን አስተዋጾ ለማበርከት ቃል በመግባት ዉይይቱ ተጠናቋል።

የጉራጌ ዞን መንግስት ኮሙዩኒኬሽን

Previous በምስረታ ጉባኤው በክብር እንግድነት የተገኙት የወልቂጤ ከተማ ከንቲባ አቶ ሙራድ ከድር ባስተላለፉት መልዕክት ሀገር የምትሰራው እና ትውልድ የሚቀረፀው በእውቀትና በጥበብ በመሆኑ ደራሲያን ትልቁን ድርሻ ይወስዳሉ ብለዋል።

Leave Your Comment

የቋንቋ አማራጭ

🇺🇸 English
🇪🇹 አማርኛ
🇪🇹 Afan Oromo