
ታህሳስ 4/2017ዓ.ም(ወልቂጤ)
የፍትህ ተቋማት ለዜጎች የሚሰጡትን አገልግሎት ውጤታማነት ጥራትና ተደራሽነት ለማጠናከር በህብረተሰቡ አመኔታን በማሳደግ በቅንጅት ሊሰሩ እንደሚገባ ተገለፀ ።
የጉራጌ ዞን ወልቂጤ ከተማ የዳኝነትና የፍትህ ሴክተር (ፍርድ ቤት ፣ፍትህ፣ ፖሊስ )ጥምረት ለማጠናከር ውይይት አካሄደ።
የወልቂጤ ከተማ አስተዳደር የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት አቶ ታጠቅ ሀይለ ማሪያም እንደገለፁት የከተማ ፍርድ ቤት አገልግሎት አሰጣጥ ውጤታማነት ተደራሽነት በማሻሻል የመንግስትና የባለድርሻ አካላትና ህብረተሰብ ቅንጅታዊ ተሳትፎን በማጠናከር የመልካም አስተዳደርና አገልግሎት አሰጣጥ ችግሮችን መፍታት እንደሚገባ ተናግረዋል ።

ህብረተሰቡ በፍርድ ቤቱ አገልግሎት አሰጣጥና መልካም አስተዳደር ላይ ለሚያነሳቸው ቅሬታዎችና ጥያቄዎች ፍርድ ቤቱ የዳኝነት ነፃነትና ተጠያቂነት ባማከለ መልኩ ብቁና ፈጣን ምላሽ በመስጠት ተገልጋዩ ህብረተሰብ በዳኝነት አገልግሎት አሰጣጥ ላይ በልዩ ትኩረት እየሰራ እንደሚገኝ ገልፀዋል።
የዳኝነት አገልግሎት ተደራሽነት ከማረጋገጥ አኳያ በከተማ አስተዳደር ፍርድ ቤት እሰከ ቀበሌ በተዘረጋው ችሎት ማዕከላት የዳኝነቱ አገልግሎት በመስጠት ህብረተሰቡ ብዙ ርቀት በመጎዝ የሚያባክነውን ጊዜና ጉልበት እንዲሁም ገንዘብ በመቆጠብ ከልማት ስራ ላይ እንዳይነጣጠል ከፍትህ አስተዋጽኦ እያበረከተ ይገኛል ብለዋል።

የከተማው ማህበረሰብ ማግኘት ያለበትን አገልግሎት ለመስጠት ችግሮችን በአጭር ጊዜ፣ በመካከለኛና በረጅም ጊዜ እቅድ በመውጣት ከፍትህ ተቋማትና ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት እየተሰራ እንደሚገኝ አስረድተዋል።
የወልቂጤ ከተማ አስተዳደር ፍትህ ፅህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ታሪኩ ዳግየ እንደተናገሩት በተቋማት ላይ ህብረተሰቡ አመኔታ በመፍጠር የፍትህ ስርዓት አገልግሎት ለዜጎች ተደራሽ ፣ቀልጣፋና ፍትሀዊ በማድረግ በከተማው የህግ የበላይነትና ሰብዓዊ መብትን ለማስከበር የፍትህ ተቋማት ሚና ከፍተኛ ነው ብለዋል።

በፍትህና በፖሊስ ተቋማት በአገልግሎት አሰጣጥ ላይ የተገኙ ውጤቶች ፣የውጭና የውስጥ ተግዳሮቶች በመለየት የቀጣይ የመፍትሔ አቅጣጫዎች ላይ የጋራ መግባባት በመፍጠር መስራት እንደሚገባ አስረድተዋል።
ሰላም የሁሉም ነገር መሰረት ነው ያሉት አቶ ታሪኩ በከተማው በተለያየ ወቅት እየተከሰቱ ግጭቶችን በህዝብና በመንግሥት ሀብትና ንብረት እንዲሁም በዜጎች ህይወት ከፍተኛ ጉዳት እንዳያስከትል ከማህበረሰቡ እና ከሌሎች ፀጥታ አካላት ጋር መልካም ስራዎች መከናወናቸውን ገልፀዋል ።
በህብረተሰቡ የሚነሡ የልማትና የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለመቅረፍ ለሚሰሩ ተግባራት ሁሉም የከተማው ህዝብ ባለቤት ሆኖ ማገዝ ይበቅበታል ያሉ ሲሆን ባለን ሀብትና እውቀት ለከተማችን ሁለንተናዊ ልማትና እድገት ሁሉም የበኩሉን ሊወጣ እንደሚገባ አስገንዝበዋል ።
በውይይት መድረኩ ላይ የተገኙት የወልቂጤ ከተማ ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባዔ ወ/ሮ ፈሰሰወርቅ ገ/ሰንበት እንደተናገሩት የተቋማት ቅንጅታዊ አሰራር መዘርጋት የህዝቦች የልማትና የመልካም አስተዳደር ችግር ለመፍታት ያለው አስተዋጽኦ ጠቀሜታው ከፍተኛ ነው ብለዋል።
የፍትህ ተቋማት ጥምረት መፍጠር በማህበረሰቡ አመኔታን በማሳደግ ፍትህና ፍትሀዊነት በማረጋገጥ የሰዎች አመለካከት እና ጣልቃ ገብነትን መከላከል መቻል አለበት ሲሉ ተናግረዋል ።
ስራዎች በተቀላጠፈና ማህበረሰባችን ከኛ የሚጠበቀውን አገልግሎት ለመስጠት የሚገጥሙንን ፈተናዎችን በፅናት በማለፍ ህጉን ሳናዛባ ተርጉሞ ማስፈን ይገባል ብለዋል።

በውይይቱ የተሳተፉ ባለድርሻ አካላት በሰጡት አስተያየት መካከል የፍትህ ተቋማት ጥምረት ስራዎች በተቀናጀና ተጠያቂነት በሰፈነበት ከግባብ ለማከናወን ያለው አስተዋጽኦ ከፍተኛ ነው ብለዋል።
ማህበረሰባችን ለዘመናት የኖረበት ባህላዊ እሴቶችን ከፍርድ ቤቶች የፍትህ ስርዓት ጋር በማቀናጀት ማከናወን እንደሚቻል አስገንዝበዋል ።
የፍትህ ተቋማት ለስራችን ከፍተኛ መስተጓጎል ሆኗል ተብለው ከተነሱ ሀሳቦች መካከል ከግብዓት አቅርቦት ችግር ከተዘዋዋሪ ችሎት (ተሽከርካሪ )፣ ህብረተሰቡ ከምስክርነትና ጥቆማ ከመስጠት አንፃር ከፍተኛ ውስንነት መኖሩ ለስራቸው እንቅፋት የሆነበት አግባብ መኖሩን አስረድተዋል ።
ቀጣይ የተሻለ ስራ በመስራት የፍትህ ተቋማት የተሰጣቸው ሀላፊነት በመውሰድ አስተማሪ የህግ ውሳኔዎች በሚዲያ ማቅረብ፣የህፃናት እና ለእናቶች የተጀመሩ ፍርዶች ቅድሚያ መስጠትና ማህበረሰቡ ለራሱና ለከተማው ሰላም ለማረጋገጥ እየተሰሩ ያሉ ስራዎች አጋዥ በመሆን ሊያግዝ ይገባል ሲሉ ተሳታፊዎች ተናግረዋል።
በውይይቱ የተሳተፉ አካላት የወልቂጤ ከተማ አመራር፣የህዝብ ክንፍ ፣ከፖሊስ ፣አቃቤ ህግ፣ፍርድ ቤት ዳኞች እንዲሁም የሀገር ሽማግሌዎች ተሳትፈዋል ።
በመጨረሻም የጉራጌ ዞን ወልቂጤ ከተማ የዳኝነትና የፍትህ አካላት ጥምረት ማጠናከሪያ ሰነድ በመፈራረም መድረኩ ተጠናቋል ።

