እናቶች በወሊድ ወቅት የሚገጥማቸው ህመምና ሞት ለመቀነስ ባለድርሻ አካት የሚያደርጉት ቅንጅታዊ አሰራር ሊያጠናክሩ እንደሚገባ ተገለፀ፡፡

ጥር 26/2017

እናቶች በወሊድ ወቅት የሚገጥማቸው ህመምና ሞት ለመቀነስ ባለድርሻ አካት የሚያደርጉት ቅንጅታዊ አሰራር ሊያጠናክሩ እንደሚገባ ተገለፀ፡፡

19ኛው የጤናማ እናትነት ወር ማስጀመሪያ የንቅናቄ መድረክ “ጥራቱን የጠበቀ የምጥና የወሊድ እንክብካቤ ለሁሉም እናት፣ ለጤናማ እናትነት” በሚል መሪ ቃል በጉራጌ ዞን ወልቂጤ ጤና ጣቢያ በተለያዩ ዝግጅቶች ተካሄዷል።

የጤናማ እናትነት ወር በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ39ኛ ጊዜ በኢትዮጵያ ደግሞ ለ19ኛ ጊዜ “ጥራቱን የጠበቀ የምጥና የወሊድ እንክብካቤ ለሁሉም እናት፣ ለጤናማ እናትነት” በሚል መሪ ቃል በጉራጌ ዞን በተለያዩ አካባቢዎች የጤናማ አናትነት ወር እየተከበረ ይገኛል፡፡

የንቅናቄ መድረኩን ያስጀመሩት የጉራጌ ዞን ጤና መምሪያ ኃላፊ አቶ አየለ ፈቀደ ወርሀ ጥር የጉራጌ ማህበረሰብ ’’አንትሮሽ’ የእናቶች ቀን የሚያከብርበት፣ ለሴቶች እንክብካቤ የሚያደርግበትና የሚያመሰግንበት ወር በመሆኑ ከእርግዝና ጋር ተያይዞ የሚከሰት የእናቶች ህመምና ሞት ለመቀነስ በትኩረት እየተሰራ ይገኛል ብለዋል፡፡

የጤናማ እናትነት ወር መከበሩ የእናቶች ህመምና ሞት አስከፊነት ግንዛቤ ለመፍጠር፣ የባለድርሻ ተሳትፎ ለማጠናከር በየ ደረጃው አጀንዳ ለማድረግ እና የእናቶች ጤንነት ለማረጋገጥ ያስችላል ብለዋል፡፡

እንደ አቶ አየለ ገለፃ እናቶች በቅድመ ወሊድ፣ በወሊድና በድህረ ወሊድ ወቅት የሚገጥማቸው የከፋ ህመምና ሞት ለመከላከል እናቶች በጤና ተቋም አገልግሎት እንዲያገኙ ግንዛቤ መፍጠር፣ የመንገድና የአምቡላንስ አገልግሎት ተደራሽነት ማረጋገጥ እና የጤና ባለሙያዎች ቀልጣፋ አገልግሎት መስጠት እንዲችሉ በቅንጅት መስራት ይገባል ብለዋል፡፡

አክለውም ኃላፊው በጤና ተቋማት ደረጃቸው የጠበቁ የእናቶች ማረፊያና የህፃናት ማቆያ ቤቶች እንዲገነቡ ማድረግ ይገባል ብለዋል፡፡

የጉራጌ ዞን ሴቶችና ህፃናት መምሪያ ኃላፊ ወ/ሮ ነጅሚያ መሀመድ በበኩላቸው የእናቶች ህመምና ሞት ለመቀነስ እተሰሩ ያሉ ስራዎች ለማጠናከር በዞኑ አበረታች ተግባራት እየተከናወኑ መሆናቸው ገልፀዋል፡፡

በተለይም በወልቂጤ ጤና ጣቢያ ከዚህ በፊት ከተገልጋዮች ይቀርብበት የነበረው ቅሬታ ለመፍታት የተወሰዱ እርምጃዎች ከፍተኛ ውጤት ያስገኙ ሲሆን በቀጣይም የመረጃ አያያዝ ጥራት በማሻሻል አንድም እናት በወሊድ ምክንያት ህመምና ሞት እንዳይገጥማት መስራት ይገባል ብለዋል፡፡

የወልቂጤ ከተማ ጤና ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ሙባሪክ ዘይኑ እንደተናገሩት እናቶች በጤና ተቋማት የሚሰጣቸው አገልግሎት ለማሻሻል እየተሰራ ሲሆን ተሞክሮዎች ለማስፋት በትኩረት መስራት ይጠበቅብናል ብለዋል።

የወልቂጤ ጤና ጣቢያ እያስመዘገበ ያለው ውጤት ከፍተኛ በመሆኑ ባለሙያዎች የጀመሯቸው ተግባራት ማስቀጠል ይገባል ብለዋል።

የመድረኩ ተሳታፊዎች የጤናማ እናትነት ወር እናቶች በቅድመ ወሊድ፣ በወሊድና በድህረ ወሊድ ወቅት ለችግር እንዳይዳረጉ ግንዛቤ ለመፍጠርና በኃላፊነት ለመስራት መነቃቃትን ይፈጥራል ብለዋል፡፡

በዕለቱ የጤናማ እናትነት ወር አስመልክቶ በቀረበው ሰነድ ውይይት ከማድረግ በተጨማሪ የወልቂጤ ጤና ጣቢያ የእናቶች ማረፊያና የህፃናት ማቆያ ክፍሎች ተጎብኝተዋል፡፡

Previous በወልቂጤ ከተማ አስተዳደር የዘመናት በህብረተሰቡ ጥያቄ ሲቀርብባቸው የነበሩ አከባቢዎች የመንገድ ከፈታ ሥራ በጉብሬ ዲስትሪክት በከተማ አሰተዳደሩ እና በህብረተሰቡ ጠንካራ ተሳትፎ የመንገድ ከፈታ ስራ ተከናወነ።

Leave Your Comment

የቋንቋ አማራጭ

🇺🇸 English
🇪🇹 አማርኛ
🇪🇹 Afan Oromo