በከተማ አስተዳደሩ የውስጥ አቅምና በህብረተሰቡ ተሳትፎ ከ3 ነጥብ 5 ኪሎ ሜትር በላይ አማራጭ የውስጥ ለውስጥ የአስፓልት መንገድ ግንባታ በሦስት ምዕራፍ ተከፋፍሎ በመከናወን ላይ መሆኑን ጠቅሰዋል።

በከተማው የነዋሪዎችን የልማት ጥያቄ የሚፈቱ የመንገድ ፕሮጀክቶች እየተከናወኑ ነው

ወልቂጤ፤ሚያዝያ 16/2017(ኢዜአ)፦በጉራጌ ዞን ወልቂጤ ከተማ አስተዳደር የነዋሪዎችን የልማት ጥያቄ የሚፈቱ የመንገድ ፕሮጀክቶች ግንባታ ሥራ እየተከናወነ መሆኑን የከተማ አስተዳደሩ አስታወቀ።

የከተማዋ አስተዳደር ከንቲባ ሙራድ ከድር ለኢዜአ እንደገለጹት፣ በከተማዋ ነዋሪዎች የመንገድ መሰረተ ልማት ጥያቄዎች ለበርካታ ዓመታት ሲነሳ ቆይቷል።

በከተማው ሰፋፊ መንገዶች አለመኖር ለከተማዋ እድገትም ማነቆ መሆኑን ጠቅሰው፣የመንገድ ችግሩን ለመፍታት ከፌዴራል መንግስትና ከህብረተሰቡ ጋር በመሆን እየተሰራ ይገኛል ብለዋል።

በከተማ አስተዳደሩ የውስጥ አቅምና በህብረተሰቡ ተሳትፎ ከ3 ነጥብ 5 ኪሎ ሜትር በላይ አማራጭ የውስጥ ለውስጥ የአስፓልት መንገድ ግንባታ በሦስት ምዕራፍ ተከፋፍሎ በመከናወን ላይ መሆኑን ጠቅሰዋል።

በመጀመሪያ ምዕራፍ በከተማው ከሰጎማ እስከ ገብርኤል ድረስ የሚዘልቅ 1 ነጥብ 2 ኪሎ ሜትር መንገድ እስከ ሰኔ ወር 2017 ዓ.ም ድረስ ተጠናቅቆ ለአገልግሎት ለማብቃት ግብ መያዙንም ጠቁመዋል።

እንደ ከንቲባ ሙራድ ገለጻ፥ በምዕራፍ ሁለትና ሦስት የተያዙ የመንገድ መሰረተ ልማት ፕሮጀክቶችን በሚቀጥለው ዓመት ለማጠናቀቅ ወሰን የማስከበርና መሰል የዝግጅት ሥራዎች ከወዲሁ እየተከናወኑ ይገኛሉ።

በወልቂጤ ከተማ ያለው ዋና የአስፓልት መንገድ አንድ ብቻ መሆኑ ለትራፊክ መጨናነቅ ስጋት ከመሆኑ ባለፈ የከተማዋ ዕድገትንም ያዘገየ መሆኑን ያነሱት ከንቲባው፥ ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታትና የትራፊክ ፍሰቱን ለማቀላጠፍ በፌዴራል መንግስት በጀት የ5 ነጥብ 6 ኪሎ ሜትር የአስፓልት መንገድ ግንባታ ሥራ እየተከናወነ መሆኑን ተናግረዋል።

የልማት ሥራው የህዝብን የዘመናት የመንገድ ጥያቄ የሚፈታ ከመሆኑንም በላይ የከተማዋን ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ዕድገት እንደሚያፋጥንም ገልጸዋል።

ከከተማዋ ነዋሪዎች መካከል አቶ ታደሰ መለሰ በከተማዋ የመንገድ መሰረተ ልማት ተደራሽነት ችግር በህብረተሰቡ ላይ ቅሬታ ሲያስነሳ እንደነበር አስታውሰው፣ አሁን እየተከናወነ ያለው ልማት የከተማዋን ነባራዊ ሁኔታ ያገናዘበ መሆኑን ተናግረዋል።

ዋና የአስፓልት መንገድን ጨምሮ የውስጥ ለውስጥ አስፓልት ግንባታ ሥራዎች መጀመራቸው የህዝብን ጥያቄ እየተመለሰ መሆኑን ያሳያል ያሉት ነዋሪው፣ መንገዶቹ የሚስተዋለውን የመንገድ መጨናነቅ ችግር ይፈተሉ የሚል እምነት እንዳላቸው ገልጸዋል።

ወይዘሮ መሰረት መለሰ በበኩላቸው፥ በተለይ ዋናው የአስፓልት መንገድ አንድ ከመሆኑ በላይ ጠባብ መሆኑ ለትራፊክ እንቅስቃሴው ምቹ እንዳልነበረ አንስተዋል።

በአሁኑ ወቅት ግንባታቸው የተጀመሩ መንገዶች ሰፋፊ በመሆናቸው ተጠናቀው ወደ አገልግሎት ሲገቡ ችግሩ ይፈታል የሚል እምነት እንዳለቸው ገልጸዋል።

ወጣት ጂላሉ ደሊል በበኩሉ፥ የከተማዋ መንገዶች ለእንቅስቃሴ አመቺ እንዳልነበሩና ይህን ለመቀየር የመንገድ መሰረተ ልማት ስራዎች መጀመራቸው መልካም መሆኑን ተናግሯል።

በከተማዋ እየተከናወኑ ያሉ የመንገድ መሰረተ ልማት

ሥራዎች በግንባታ ሂደት ለወጣቱ የሥራ ዕድል እየጠሩ መሆናቸውንም ተናግሯል።

Previous በወልቂጤ ከተማ እየተሰራ ያለው 25 ኪሎ ሜትር የኮሪደር ልማት ስራ የጉራጌ ዞንና የወልቂጤ ከተማ አመራሮች በተገኙበት የእስካሁኑ አፈጻጸም ተገምግሟል።

Leave Your Comment

የቋንቋ አማራጭ

🇺🇸 English
🇪🇹 አማርኛ
🇪🇹 Afan Oromo