ትልቁ የባህል መሰረት የሆኑት የሀይማኖት አባቶችንና የሀገር ሽማግሌዎችን ማክበርና መታዘዝ የሁሉም ዜጋ ግዴታ መሆን መሆን እንዳለበት ተገለጸ።

የወልቂጤ ከተማ አስተዳደር ከሀይማኖት አባቶችና ከሀገር ሽማግሌዎች ጋር በሠላም ዙሪያ የውይይት መድረክ አካሄደ::

የውይይቱ ዋና ዓላማም በከተማችን ያለውን የልማትና የመልካም አስተዳደር ችግሮችን በጋራ በመወያየት ቀጣዩን ጊዜ የተሳካ ለማድረግና በአካባቢዉ የሚፈለገዉ ዉጤት እንዲመጣ ለማድረግ ኦንደሆነም የወልቂጤ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ሙራድ ከድር ገልጸዋል::

ወልቂጤ ከተማ የብዙ ታሪክ ትውፊትና በማህበራዊ ጉዳዮች ላይ ፋና ወጊ መሆኗንና በተለያዩ ጊዜያት ዕዉቅና ያገኘች ከተማ እንዲሁም የሁሉም መስመር ኮሪደርና የሁሉም ማረፊያ እንደሆነችም አስታዉሰዋል።

ነገር ግን በከተማዋ በሚፈለገው ልክ ልማት እንደሌለና ከሌሎች አቻ ከተሞች እኩል ባለማደጓ ቅር መሰኘታቸውን ገልጸዉ ቀጣይ በተባበረ ክንድ ሁሉም ለከተማዉ እድገት ትኩረት በመስጠት የሚፈለገዉ ለዉጥ እንዲመጣ በቅንጅት ይሰራል ብለዋል።

ወልቂጤ ከተማ ሠላሟና ደህንነቷ የተጠበቀ ዜጎቿ በነጻነት የሚንቀሳቀሱባትና ያለምንም የብሔር ልዩነት ሁሉም በጋራ ሰርቶ እንዲኖር ማድረግና ከእኔነት ይልቅ እኛነትን ለመፍጠር የሀይማኖት አባቶች የሀገር ሽማግሌዎች የከተማው አመራር እንዲሁም ሁሉም ባለድርሻ አካላት መስራት እንዳለባቸው ጠቁመዋል::

የሀይማኖት አባቶችና የሀገር ሽማግሌዎች እንዲሁም ታላላቆች ትውልድን የሚመክሩ የሚገስጹ ህገ ወጥ ተግባራትን የሚያስቆሙ ሠላምን የሚሰብኩ እንዲሁም የሚያውኩትን አካላትን አሳልፎ በመስጠት ማገዝ እን ዳለባቸዉ አሳስበዋል።

ወልቂጤ በመጠላለፍና በመቧደን በጎሳና በብሔር በሰፈር የተመሠረተ አመራር ሳይሆን ተልዕኮን የሚሸከም ችግርን የሚጋፈጥና የመፍትሔ አካል የሆነ አመራር ያስፈልጋታል ሲሉም አንስተዋል::

የአንድ ከተማ ዕድገት የሚወሰነው በሚሰበሰበው ገቢ ልክ እንደሆነ ገልፀው እኛም የምንመኛትን ወልቂጤ ለመፍጠር የገቢ አሰባሰባችንን አጠናክረን በመስራትና በዘርፍ የተሰማሩ አካላት ትኩረት ሊሰጡት እንደሚገባም አመላክተዋል።

በከተማዉ ላይ በርካታ ተጀምረው ያላለቁ የመሰረተ ልማት ፕሮጀክቶች መኖራቸው አንዱ ችግር በመሆኑን ሁሉም የድርሻውን በመወጣት ለከተማዉ እድገትና ልማት ሃላፊነቱን ሊወጣ ይገባል ብለዋል፡፡

ከልማት አንጻር የተነሱትን ሀሳቦች በግብአትነት በመውሰድ የዕቅድ አካል በማድረግ ለመሥራት በቁርጠኝነት መነሳታቸውን ክቡር ከንቲባው አንስተዋል።

የወልቂጤ ከተማ ብልጽግና ፓርቲ ጽህፈት ቤት ሀላፊና ዋና የመንግስት ተጠሪ የሆኑት አቶ ታደለ በቀለ በበኩላቸው ከአባቶቻችን የተሰጡንን አስተያየቶች በመውሰድ እንደየቅደም ተከተላቸው በጋራ ሆነን የምንሰራ ይሆናል ብለዋል።

አያይዘውም ወልቂጤ ሁሉንም እንድትጠቅም ለማድረግ የሁላችንም መተጋገዝ ወሳኝ ነው ሲሉ ተናግረዋል።

የሰላምም ሆነ የልማት ስራዎች የሁላችንም ትብብርና ቅንጅት የሚጠይቅ በመሆኑ በምንሰራቸው ስራዎች ላይ ህብረተሰቡን ያሳተፈ ስራ መስራት እንደሚገባም አቶ ታደለ ጠቁመዋል።

በውይይቱ የተገኙ ተሳታፊዎችም ከተማችን ዕድገትና መለወጥ ሁላችንም የሚጠበቅብንን ለማድረግ ዝግጁ ነን ሲሉ ሀሳባቸውን ገልጸዋል::

በከተማዋ በሚሰሩ ሥራዎች ላይ የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ለማበርከት ዝግጁ መሆናቸውንም ጠቁመዋል።

አመራሩና ህዝቡ ተቀራርቦ በመስራት የህብረተሰቡን ተሳትፎ ማጎልበት ከተቻለ የከተማዉን ሰላምና ልማት ማሳደግ እንደሚቻል በጉራጌ ዞን የወልቂጤ ከተማ የሀይማኖት አባቶችና የሀገር ሽማግሌዎች ገልጸዋል፡፡

Previous መስከረም 8/2017 ዓ.ም

Leave Your Comment

የቋንቋ አማራጭ

🇺🇸 English
🇪🇹 አማርኛ
🇪🇹 Afan Oromo