በህዝቡ የሚነሱ የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ምላሽ ለመስጠት የኢኮኖሚና የማህበራዊ ዘርፍ ተቋማት ሚና ከፍተኛ መሆኑ የወልቂጤ ከተማ አስተዳደር ገለፀ።
ጥር 26/2018ዓ.ም [ወልቂጤ ]
የወልቂጤ ከተማ ምክር ቤት 2ኛ ዙር 13ኛ አመት 48ኛ መደበኛ ጉባዔ አካሄደ።

የወልቂጤ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ሙራድ ከድር እንደገለፁት በህዝቡ የሚነሱ የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ምላሽ ለመስጠት የኢኮኖሚና የማህበራዊ ዘርፍ ተቋማት ሚና ከፍተኛ መሆኑን ገልጸዋል ።
የከተማዋ ልማትና ብልፅግና ለማረጋገጥ እና በኢኮኖሚ ዘርፍ የሚሰሩ የገቢ አሰባሰብ ስርዓታችን በማጠናከር የውስጥ ገቢን ማስፋት እንደሚገባ ተናግረዋል።
በ2018 በጀት አመት በማዘጋጃና በመደበኛ ገቢ ከ1.5 ቢሊዮን ብር ለመሰብሰብ እቅድ ታቅዶ እየተሰራ ነው ያሉ ሲሆን ከባለፉ አመታት ተመሳሳይ ወቅት ሲነፃፀር የተሻለ መሆኑ አንስተዋል። ሆኖም ከህዝባችን ከሚነሱ የልማት ጥያቄዎች አንፃር የኢኮኖሚ ሀብት የገቢ ስርዓታችን ውስንነት ለመቅረፍ ሁሉም በሀላፊነት ሊሰራ ይገባል ብለዋል።

የገቢ አቅማችን ለማሳደግ ማህበረሰባችን በግብይት ወቅት ደረሰኝ የመጠየቅ ባህሉም ማሳደግ እንዳለበትም አንስተዋል።
በከተማችን የተጀመሩ ፕሮጀክቶች በፍጥነትና በጥራት በማጠናቀቅ የኮሪደር ልማት፣የአስፓልት ስራ፣ የማህበረሰብ የመድሀኒት ቤት፣ ከተማዋን የሚመጥን የከንቲባ ፅህፈት ቤት ግንባታ እንዲሁም የኢኒሼቲቭ ስራዎች በበጀት አመቱ መልካም አፈፃፀም ተመዝግቧል ሲሉ አብራርተዋል ።

ቀጣይ ህዝቡ የሚፈልገው ልማት ለማሳለጥ የትምህርት ቤት፣የገበያ ማዕከላት ፣የመንገድ ከፈታ፣የጌጠኛ ድንጋይ ምንጣፍ፣የመልሶ ጥገና ስራዎች እንዲሁም የመሶቦ አገልግሎት ተግባራት በልዩ ትኩረት ይሰራል ብለዋል።
የኑሮ ውድነት ለማረጋጋት የሰንበት ገበያ በማጠናከር ሸማቹና አምራቹ ቀጥተኛ የገበያ ትስስር በመፍጠር የተሰሩ ስራዎች መኖራቸውን ገልፀው ካለው የህዝብ ፍላጎት የተስተዋሉ ክፍተቶች እየተለዩ የተሻለ ስራ እንሰራለን ብለዋል።

እንደሀገር የገጠመው የነዳጅ አቅርቦት ችግር በፍትሀዊነት ተደራሽ ለማድረግና ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በቅርበት እየተሰራ ነው ሲሉ አቶ ሙራድ ተናግረዋል።
ሰላም የሁሉንም ነገር መሠረት ነው ያሉት ከንቲባው የምንፈልገው ልማትና እድገት ለማሳለጥ በሰላም ዙሪያ የተጀመሩ ጠንካራ ስራዎች በማጠናከር የሚስተዋሉ ክፍተቶች ላይ በቅንጅት መስራት ይጠበቅብናል ብለዋል።

የወልቂጤ መልካም ገፅታ በመገንባት ለነዋሪዎች ምቹ ለማድረግና ከቆሻሻ የፀዳች ከተማ ለመፍጠር በህዝብ ተሳትፎ በባለቤትነት መስራት ይገባል።
የወልቂጤ ከተማ ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባዔ ወ/ሮ መንዚላት አህመድ በጉባኤ እንደተናገሩት የከተማው ማህበረሰብ የልማቱ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የአስፈጻሚ አካላት ቁጥጥርና ክትትል ስራዎች በማጠናከር የመንግስትና የህዝብ ሀብት በአግባቡ ጥቅም ላይ በማዋል እና ለስራው ውጤታማነት የምክር ቤት አባላት ልዩ ተሳትፎ ከፍተኛ ነው ብለዋል።

ምክር ቤቶች የመፈፀምና የማስፈፀም አቅማቸውን በየጊዜው በማሳደግና በማጎልበት የተሰጣቸውን ህዝባዊና መንግስታዊ አደራ በብቃት እንዲወጡ የሚያስችላቸውን የተሻለ አሰራሮችንም በተጨባጭ መተግበር የሚችሉበትን ክህሎት መፍጠር አስፈላጊ መሆኑንም አብራርተዋል ።
ከምክር ቤት አባላት ከተነሱ አስተያየቶች መካከል በከተማ አስተዳደሩ በሁሉም ዘርፍ የህዝቡ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በርካታ የልማት ስራዎች መከናወናቸው ተናግረዋል።
በከተማዋ እየተሰሩ ያሉ የልማት ትልልቅ ፕሮጀክቶች በተቀመጠላቸው ጊዜ ተጠናቀው ለሚፈለገው አገልግሎት እንዲውሉ የክትትል ስራዎች ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል።
ሰላም የሁሉም ነገር መሰረት በመሆኑ ለሰላማችን እጦት ምክንያት የሆኑ ችግሮች በመለየት የፀጥታ መዋቅሩ ከህዝቡ ጋር በቅንጅት ሊሰራ እንደሚገባ ገልፀዋል።

እንዲሁም በከተማ የሚገኘው የወልቂጤ ዩንቨርስቲ ለማህበረሰቡ እየሰራቸው ያሉ ስራዎች በማሳደግ በተደጋጋሚ በህዝቡ የሚነሱ የልማት ስራዎች ላይ ተሳትፎ በማድረግ የበኩሉን ሊወጣ ይገባል ሲሉ የምክር አባላት አንስተዋል።

የዉሃ ምርትና ፍትሀዊ ስርጭት ፣የብድር አመላለስ መቀዛቀዝ ፣የታክሲ ስምሪት ችግር፣ ፍትሀዊ የነዳጅ ስርጭት ችግር፣በኢንተርፕራይዝ የተሰማሩ አምራቾች የገበያ ትስስር አለመኖር፣በከተማዋ ህገወጥ እንቅስቃሴ ፣የንግድ እቃዎችን ላይ ጭማሪ መኖር፣የከተማ ግብርና የቦታ ዝግጅት ማነስ፣የደረቅና ፈሳሽ ቆሻሻ አወጋገድ ስርዓት ችግር ልዩ ትኩረት በመስጠትና የህዝብ ተሳትፎ በማሳደግ በቅንጅት ልንሰራ ይገባል ሲሉ የምክር ቤት አባላት በጉባዔው አንስተዋል ።
የወልቂጤ ከተማ ምክር ቤትና ከተማ ፍርድ ቤት የ2018ዓ.ም የ2ኛ ሩብ አመት እቅድ አፈፃፀም ሪፖርት ቀርቦ ውይይት ተደርጓል።
በመጨረሻም የወልቂጤ ከተማ ምክር ቤት ሞዴል ምክር ቤት አባላት እውቅና ተሰጠ።

