ጉራጌ በህይወት ዘመኑ ሁሉ ባህላዊ ሸንጎ ያስቀመጣቸው ማህበራዊ ስርዓቶችና ድንጋጌዎችን ጠብቆ ከሁሉም ጋር በሰላም፣በመቻቻልና በፍቅር እንዲኖር ካስቻሉት ባህላዊና መንፈሳዊ እሴቶች አንዱ ጡር ይባላል፡፡ በጉራጌ ታሪክ ጡር በሁለት መንገድ እንደሚገባ ይታወቃል፡፡ አንዱ መንገድ ሰዎች በብዙ በደል በብዙ መገፋትና ስቃይ ታግሰው አምላኬ ለትውልዴ ለዘሬ የተሻለ ቀን ያመጣል፣ስለዚህ በእኔ ላይ የሚፈፀመው ግፍ አንድ ቀን ያቆማል ብለው ተስፋ በማድረግ የሚያገኙት መልካም ነገር ነው፡፡ በዚህ ሁሉ ትዕግስት ተበዳዩ ለበዳዩ ሁልጊዜ በአምላኩ ፊት ቆሞ ‹‹ኤበርየ ጡር የህርብኸ፣ ጡራኸ ይያ ሸመነ የግባ›› በአማርኛው ‹‹እገሌ ጡር ይሁንብህ ጡርህ እኔ ቤት ይግባ›› በማለት ከአንደበቱ ቃል አውጥቶ ይናገራል፡፡ እግዚአብሔር አምላክም የምስኪኖች ወዳጅ ነውና የችግረኛችን ጩኸት ከመስማት ዝም ያለበት ጊዜ እንደሌለ አባቶች ይናገራሉ፡፡ በዚህ ሁኔታ በእግዚአብሔር ጊዜ የበዳዩ ቤት ጡር ወደ ተበዳዩ ቤት እንደሚዞር የባህላዊ ሸንጎ አካላት ይናገራሉ፡፡ ይህንን እውነታ በምሳሌ ሲያስረዱ አንዳንድ ጊዜ አንድ አያት የወለዳቸው ቤተሰቦች መሀል እንኳ ባላቸው ሀብትና የልጅ ብዛት ትልቅ ልዩነት ይከሰታል፡፡ የቀደሙት የፖለቲካ ስርዓቶች ሴቶችን ከንብረትም ሆነ ከመሬት ባለቤትነት ያገሉ የነበረና ባህሉም በራሱ ለወንዶች ያደላ የነበረ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ብዙ ወንድ ልጆች የወለደ አባት ወንድ ሳይወልድ የቀረን የወንድሞቹ ሴት ልጆች በመግፋት መሬቱን ለራሱ በመከለል በመጨረሻም ለራሱ ልጆች ያከፋፍላል እንበል፡፡ ይሄ አይነቱ መሬት በባህሉ የፈነጠበያር አፈር ይሉታል፡፡ ሴቶች ልጆቹም በሀይል መሬታቸው ሲቀሙ ማስጣል ስለማይችሉ መስማት ለሚችለው አምላክ አባታችንና አጎታችን ከአንድ እናትና አባት የተገኙ ሁለት ወንድማማቾች ነበሩ ዛሬ ግን አባታችን ወንድ ባለመውለዱ የተነሳ እኛን ሴቶች ልጆቹን ገፍቶ መሬታችን ወሰደ ስለዚህ እግዚአብሔር ሆይ አንተ አይን አለህናይህን በደሉን እይበት ጡር ይሁንበት በእኛ ላይ እንደሆነብን በተራ በእርሱም ቤት እንዲሁ ይሁንበት እኛም ዛሬ በተገፋንበትና በተበደልንበት ለልጆቻችንና ለዘራችን ጡር ይግባልን ይላሉ፡፡ ማንም የዘራውን ማጨዱ አይቀርምና በዳይ አጎት የእጁን ዕንደሚያገኝ ሽማግሌዎች ይናገራሉ፡፡

ሁለተኛው ጡር የሚወጣበት ሁኔታ ደግሞ አንድ ሰው አባት፣አያት፣ቅድመ አያት ወዘተ ያቆዩለትን ጡር እርሱ ስልጣኑን ወይም ሃብቱን ያለ አግባብ ተጠቅሞ በሰዎች ላይ ግፍ በመፈፀምና የሰዎችን መብት በመግፈፍ በሚፈፅመው በደል የተነሳ በጥቂት ሰዓታት ውስጥ ቤቱ የቆየውን ጡር ገፍቶ ሲያስወጣው ሲሆን ይህም በጉራግኛ ‹‹ጡር ተቤተህኖ ኦነሞ ወጣም›› (ጡር ከቤታቸው ጮሆ ወጣ) ይባላል፡፡ጉራጌ አንዱ ተበዳይ በሌላው ጊዜ በሰጠው ሰው ወይም ጉልበተኛ ሲበደል ሲያይ ለተበዳዩ ‹‹ጡር የህርኸ›› ‹‹ጡር ይግባልህ›› ሲለው ለበዳዩ ‹‹ጡር የህርብኸ›› ማለትም፡- እግዚአብሔር የሰጠህን መልካም ነገርህና ጸጋህ ካንተ ላይ አንስቶ ይውሰድ እንደማለት ነው፡፡ ይህ ደግሞ ጉራጌን በህይወት ጉዞው ነገሩ ሁሉ በእግዚአብሔር ዘንድ የተገለጠና ሊሰወር እንደማይችል በመረዳት በፍርሃት፣ በቅንነትና በትዕግስት እንዲመላለስ አስችሎታል፡፡ስለሆነም ባህሉን ጠንቅቆ የሚያውቅ በየትኛውም ማዕዘን የሚኖር ጉራጌ ነፍስ ማጥፋትን፣ በሀሰት መመስከር፣ቤት ማቃጠል፣ግፍ መስራት፣ድንበር ማለፍ፣ክህደትን፣የሰው ሀብት መንጠቅ …ወዘተ በእጅጉ ይጠየፋል፡፡ የባህል እሴት የሆነው ጡር ሰዎች ከክፉ እንዲርቁና መልካሙን እንዲያደርጉ ያደርጋቸዋል፡፡የጉራጌ ዞን ባህል እና ቱሪዝም መምሪያ

