
ሰኔ 25/2O16 ዓ/ም [ወልቂጤ]
በወልቂጤ ከተማ በተለያዩ ዘርፎች የተሰሩ የልማት ስራዎችን ጠንካራ ጎኖችን በማስቀጠል በ2O17 በጀት አመት የተሻለ የልማት ስራ ለመስራት መዘጋጀት እንደሚገባ የወልቂጤ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ እንዳለ ስጦታው ገለፁ።
በከተማ አስተዳደሩ የተሰሩ ልዩ ልዩ የልማት ስራዎች ከዞንና ከከተማ አስተዳደሩ በተውጣጡ አመራሮች በዛሬው እለት ተጎብኝቷል።
በወልቂጤ ከተማ አስተዳደር በመንገድ፣ በኢንቨስትመንትና በሌሎችም በህብረተሰቡ፣ በመንግስትና በግል ባለሃብቶች የተሰሩ ልማቶች በባለድርሻ አካል ተጎብኝቷል።

የወልቂጤ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ እንዳለ ስጦታው የጉብኝቱ ጠንካራ ጎኖችን በማስቀጠል ውስንነቶች ላይ በቀጣይ ትኩረት ሰጥቶ ለመስራት ዓላማ ያደረገ ነው።
በዚህ ረገድ በመንገድ ልማቱ ይሁን በኢንቨስትመንት እንዲሁም ሌሎች ዘርፎች ከዕቅድ በላይ መስራት እንደተቻለም አስረድተዋል።

ቀደም ሲል ማህበረሰቡ ቅሬታ ያነሳባቸው የነበሩ መንገዶችን ከመክፈት በተጨማሪ የዲች፣ የጌጠኛ ድንጋይ ንጣፍና በርካታ ማህበረሰቡን የሚጠቅሙ ተግባራት እንደተከናወነ ተናግረው በተለያዩ ዘርፎች የተመዘገቡ ምርጥ ተሞክሮዎችን በመውሰድ በ2O17 በጀት አመት የተሻለ የልማት ስራ ለመስራት መዘጋጀት እንደሚያስፈልግም ገልፀዋል።

በጉብኝቱ የተሳተፉት የጉራጌ ዞን ኢንቨስትመንትና ኢንደስትሪ ልማት መምሪያ ሃላፊ አቶ ናስር ሐሰን በከተማው የኢንቨስትመንትን ጨምሮ በልዩ ልዩ የልማት ስራዎች ላይ የተሻለ እንቅስቃሴ እንዳለ በጉብኝቱ መመልከታቸው ገልፀዋል።
በከተማ ቀደም ሲል ቦታ ተረክበው ወደ ስራ ያልገቡ ኢንቨስተሮች ስራ እንዲጀምሩ የተደረገበት ሁኔታም አበረታች ነው ብለዋል።
የወልቂጤ ከተማ አስተዳደር ማዘጋጃ ቤታዊ አገልግሎት ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ይብጌታ ንጋ ማዘጋጃ ቤቱ ያለውን የሰው ሃይል ተጠቅሞ የታቀዱ ስራዎች በዕቅዳቸው እንዲሰሩ እርብርብ ሲያደርግ ቆይቷል ብለዋል።

በከተማው ያለው አመራርና የማዘጋጃ ቤቱ ባለሙያ በሰራው የቅንጅት ስራ በአመቱ በማቺንግ ፈንድና ሌሎችም አማራጮች በመጠቀም ለመስራት የታቀዱ የመንገድ መሰረተ ልማት ስራዎች ውጤታማ በሆነ ሁኔታ መስራት እንደተቻለ ገልፀዋል።
በ2O ሚሊዮን ብር ማቺንግ ያደሩና አዳዲስ 14 ፕሮጀክቶች ተሰርተዋል ያሉት ሃላፊው ከ2O ኪሎ ሜትር በላይ የጠጠር መንገዶች እንደተሰሩም ጠቁመዋል።

በዚህ ረገድ የማህበረሰቡ ተሳትፎ ጥሩ እንደነበረ አስታውሰው በኮንስትራክሽን ዘርፍም በሆቴል ግንባታ የተሰማሩ ባለሃብቶች ችግሮቻቸው ተቀርፈው ግንባታ እንዲጀምሩ እንደተደረገም ተናግረዋል።
የወልቂጤ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ግርማ ንቅበሽዋ በ2O16 በጀት አመት በካፒታል ፕሮጀክት የተሰሩ የልማት ስራዎች በጊዜ፣ በጥራትና በፍጥነት ስለመሰራታቸው ለማረጋገጥ የተደረገ ጉብኝት ነው ብለው በዚህም ብዙ ስኬቶች የታዩበት ነው ብለዋል።

ካፒታል ፕሮጀክቶች ማህበረሰቡ ተጠቃሚ የሚያደርጉ ናቸው ያሉት አቶ ግርማ የከተማው እድገት የሚያፋጥኑ መሆናቸውም ጠቁመዋል።
በ2O16 በጀት አመት ፕሮጀክቶች በጥራትና በፍጥነት እንዲሰሩ ክትትል በመደረጉ ውጤታማ መሆን እንደተቻለና ይህም በቀጣይ በጀት አመት ለመስራት የታቀዱ ዕቅዶች በውጤታማነት እንዲሰሩ በማድረግ ረገድ አስተዋጽኦ አለው ብለዋል።
በጉብኝቱ የተሳተፉት አካላት በሰጡት አስተያየት በጌጠኛ ድንጋይ ንጣፍ፣ በዲች ግንባታና በሌሎች በመንገድ መሰረተ ልማትና በአገልግሎት ዘርፎች እየተሰሩ የሚገኙ ስራዎች ውጤታማ መሆናቸውን ተናግረዋል።
በቀጣይም ፕሮጀክቶች እንዳይዘገዩና በተሻለ ጥራት እንዲሰሩ በዚህ ልምድ ወስዶ የተሻለ ስራ መስራት እንደሚጠበቅም ገልፀዋል።

በጉብኝቱ የጉራጌ ዞን ኢንቨስትመንትና ኢንደስትሪ ልማት መምሪያ ሃላፊ አቶ ናስር ሐሰን፣ የወልቂጤ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ እንዳለ ስጦታው፣ የወልቂጤ ከተማ አስተዳደር ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ አብድልበር ሰይድ እና በከተማው በየደረጃው የሚገኙ አመራሮች ተሳታፊ ሆነዋል።

