የወልቂጤ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ጽህፈት ቤት ለቅድመ አንደኛ ደረጃ መምህራን የጉራጊኛ ቋንቋ ትምህርት ስልጠና ተሰጠ።
ቋንቋ ለተወላጅ ብቻ የተሰጠ ባለመሆኑና ድንበር የሌለው መግባቢያ ስለሆነ ቋንቋን ሳንንቅ በቋንቋ ብንማር ትምህርት ሊከብደን አይችልም፤ በተጨማሪ ቋንቋ ለህፃናት ባህልና እሴት ለማስጨበጥ ትልቁ መሳሪያ ነው ሲሉ የወልቂጤ ከተማ ትምህርት ጽህፈት ቤት ሃላፊ ወይዘሮ መንዚላት አህመድ ገልጸው።
አምና በ20 የቅድመ መደበኛ ትምህርት ቤቶች ሙከራ መደረጉን አስታውሰው በዘንድሮው ደረጃ በ13 የቅድመ መደበኛ ትምህርት ቤቶች እንደሚጀምር ገልጸዋል።

አያይዘውም ልጆቻችን የጉራጊኛ ቋንቋ ተምረው ቋንቋቸውን በህገ-መንግሥቱ በፈቀደላቸው መሠረት መብታቸው የተጠበቀ ቢሆንም ወደ ተግባር ከመግባት ጋር ተያይዞ መዘግየቱን ተናግረዋል።
የጉራጊኛ ቋንቋን በስርአተ ትምህርት ተካቶ መሰጠቱ የመጀመሪያ በመሆኑ ለውጤታማነቱ የወላጆችና የመምህራን ተሳትፎ እጅግ አስፈላጊ መሆኑን የትምህርት ጽህፈት ቤት የስርአተ ትምህርት ቡድን መሪ የሆኑት አቶ አብዶ መሀመድ ገልጸዋል።
አንዳንድ የስልጠናው ተሳታፊ የሆኑ መምህራኖች እንደገለፁት ቋንቋ የማልማት ስራ የሚሰራው የቅድመ መደበኛ ትምህርት ቤቶች እንደመሆኑ መጠን እኛም ከስልጠናው ያገኘነውን ግንዛቤ አዳብረንና አስፍተን ባህልና እሴታችን ማሳደግ መቻል አለብን ብለዋል።
በአፍ መፍቻ ቋንቋ ማስተማር የመጀመሪያ ጊዜ ሙከራ እንደመሆኑ መጠን በመማር ማስተማሩ ሂደት ሊገጥሙን የሚችሉ ችግሮች መፍትሔ እየሰጠን የምናስቀጥል ይሆናል ሲሉ ጠቁመዋል።
በመጨረሻም የወልቂጤ ከተማ ትምህርት ጽህፈት ቤት ሃላፊ ወይዘሮ መንዚላት አህመድ ሁሉም ሰልጣኞች ዛሬ የተሰጠው የአፍ መፍቻ ቋንቋ ስልጠና የራስ የሆነ ስልት በመጠቀም ሁሉም ልጆች ቋንቋቸው አዳብረው በትምህርታቸው ውጤታማ ከመሆን ባለፈ እሴታቸው ማሳደግ የሚችሉት በእናንተ ሲታገዙ መሆኑን ተረድታችሁ ሀላፊነታችሁን እንድትወጡ ሲሉ ጥሪ አስተላልፈው ስልጠናው ተጠናቋል።

