መስከረም 24/2016 ዓ.ም (ወልቂጤ)
የጉራጌና የኦሮሞ ህዝቦች የቆየ የእርስ በርስ ግንኙነት የበለጠ ለማጠናከር በልማቱ ስራም በትኩረት እንደሚሰራ የኦሮሚያ ክልል ርእሰ መስተዳድር ፕሬዝዳንት አቶ ሽመልስ አብዲሳ ተናገሩ።
በኦሮሚያ ክልል መንግስት የገንዘብ ድጋፍ በ80 ሚሊየን ብር የተገነባው የጉስባጃይ ኢፋ ቦሩ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተመርቆ መማር ማስተማሩ ጀመረ።
የኦሮሚያ ክልል ርእሰ መስተዳድር ፕሬዝዳንት አቶ ሽመልስ አብዲሳ በመድረኩ ተገኝተው እንደተናገሩት የጉራጌ ህዝብ ድንበር የማይገድበው፣ስራ ሳይንቅ የሚሰራ፣ቁጠባን ያስተማረ፣ታታሪ ህዝብና ለሌሎች አረያ የሚሆን ትልቅ ህዝብ በመሆኑ ለዚህ ህዝብም አድናቆት አለኝ ብለዋል።
ህዝቡም መሰል አይነት አኩሪና አስተማሪ ባህሎቹና የስራ ታታሪነቱን አጠናክሮ ማስቀጠል እንዳለበት መክረዋል።
በርካታ በኦሮሚያ ክልል የሚኖሩ የጉራጌ ተወላጆች በንግድና በተለያዩ ስራዎች በመሰማራት ለክልሉ መልማት ከፍተኛ ሚና እየተጫወቱ እንደሆነ አስታውቀው ለነዚህም አስፈላጊውን ድጋፍና እንክብካቤ እንደሚደረግ ገልጸዋል።
የጉራጌና የኦሮሞ ህዝቦች ለሀገር ግንባታው በጋራ የታገሉ፣ተቻችለውና በፍቅር የኖሩና የሚኖሩ በመሆናቸው የእርስ በርስ ግንኙነቱ የበለጠ እንዲጠናከር በልማቱ ስራም በትኩረት እንደሚሰራ አቶ ሺመልስ አሳታውቀዋል።
አክለውም በክልሉ በሚሰሩ መንኛውም የልማት ስራዎች የኦሮሚያ መንግስት እገዛ እንደሚደረግ አስገንዝበዋል።
ኢትዩጵያዊያን ከሚያለያዩን ጉዳዮች አንድ የሚያደርጉን ነገሮች ይበልጣሉ ያሉት ፕሬዝዳንቱ ልዩነቶቻችን በማጥብ ለሀገራችን እድገት በጋራ መስራት ይጠበቅብናል ብለዋል አቶ ሽመልስ።
የማእከላዊ ኢትዩጵያ ክልል ርእሰ መስተዳድር አቶ እንዳሻው ጣሰው የኦሮሚያ ክልል መንግስት ሙሉ ወጪውን በመሸፈን የጉስባጃይ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ሰርቶ በማስረከቡ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
የኦሮሚያ ክልል መንግስት በተለያዩ ክልሎች መሰል አይነት በልማትና በሰላም እያደረጋቸው ያለው ስራዎች የሚበረታታ ነው ያሉት ክቡር እንዳሻው በማእከላዊ ክልልም የተጀመሩ ስራዎች ተጠናክረው ሊቀጥሉ ይገባል ብለዋል።
በርካታ የጉራጌ ተወላጆች በኦሮሚያ ክልል የሚኖሩ ሲሆን የክልሉ መንግስትም ለብሄሩ ተወላጆች አስፈላጊውን ድጋፍና እንክብካቤ እንዲደረግላቸው ጠይቀዋል።
የኦሮሚያ ክልል የጸጥታና ፍትህ ክላስተር አስተባባሪ ኮሚሽነር ጄነራል ከፍያለው ተፈራ በበኩላቸው የጉራጌና የኦሮሞ ህዝቦች ካላቸው ጥብቅ ትስስር አንጻር መሰል አይነት የልማት ስራዎች በጋራ ሊሰሩ ይገባል።
መሰል አይነት የትብብር ስራዎች ሲሰሩ ትውልዱ የሀገር ባህልና ታሪክ እንዲያውቅ፣የጋራ አስተሳሰብና አብሮነትን የሚያጠናክር ትውልድ ይፈጠራል ያሉት ኮሚሽነር ከፍ ያለው ልማትን ለማስቀጠል ሁሉም ለሰላሙ ትኩረት ሰጥቶ ሊሰራ እንደሚገባ መክረዋል።
የኦሮሚያ ክልል ኢንጅነሪንግ ኮርፖሬሽን ዋና ዳይሬክተር አቶ ዳዊት በቀለ አጠቃላይ ስለ ግንባታው በሰጡት ገለጻ ትምህርት ቤቱ 8 ብሎኮች ያሉት ሲሆን 46 ዘመናዊ የመማርያ ክፍሎች፣የአስተዳደር ህንጻ፣የአይ ሲቲ ፣የላብራቶሪ፣የትምህርት ማበልጸጊያ፣የወርክ ሾፕ፣የላይብረሪ፣የወንድና የሴት መጸዳጃ ክፍሎችና ሌሎችም በውስጡ የያዘ ሲሆን 80 ሚሊየን ብር ወጪ ተደርጎበታል ብለዋል።
አቶ ይታገሱ አርጋውና አቶ ሙኒር አወል የአካባቢው ነዋሪዎች ሲሆኑ ትምህርት ቤቱ መገንባቱ ተማሪዎች ከዚህ በፊት ይደርስባቸው የነበረ እንግልት የሚቀርፍ ሲሆን በቀጣይ በትምህርት ጥራትና በተማሪዎች ስነምግባር ላይ በትኩረት መስራት ያስፈልጋል ነው ያሉት።
በመጨረሻም ለትምህርት ቤቱ ግንባታ አስተዋጾ ላደረጉ አካላት እውቅናና ሽልማት የተሰጠ ሲሆን ለኦሮሚያ ክልል ርእሰ መስተዳድር ፕሬዝዳንት ለአቶ ሺመልስ አብዲሳ ከአካባቢው ማህበረሰብ የፈረስ ጉክስ ተበርክቶላቸዋል ሲል የዘገበው የጉራጌ ዞን የመንግስት ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች መምሪያ ነው።






