በወልቂጤ ከተማ የታክሲ ትራንስፖርት አገልግሎት መጀመሩ የጉራጌ ዞን ትራንስፖርት እና መንገድ ልማት መምሪያ አስታወቀ።
በከተማው የተጀመሩው የታክሲ ትራንስፖርት አገልግሎት ይስተዋል የነበረው የተሳፋሪው እንግልትና ያላስፈላጊ የገንዘብ ወጪ የሚያስቀር መሆኑ ተሳፋሪዎች ገለጹ።

በዛሬው እለት በወልቂጤ ከተማ ከአቢሲኒያ ባንክ እስከ ጉብሬ ክፍለ ከተማ መናኸሪያ ድረስ የታክሲ ትራንስፖርት አገልግሎት በይፋ ተጀምሯል።

የጉራጌ ዞን ትራንስፖርት እና መንገድ ልማት መምሪያ ኃላፊ አቶ ሙራድ ከድር የታክሲ ትራንስፖርት አገልግሎት ባስጀመሩበት ወቅት እንዳሉት በወልቂጤ ከተማ አቢሲኒያ ባንክ እስከ ጉብሬ ክፍለ ከተማ መናኸሪያ ባለው መንገድ ከፍተኛ የትራንስፖርት ፍሰት ካለባቸው ስምሪቶች አንዱ መሆኑን ገልጸው በ25 ብር ታሪፍ ከ12 በላይ የታክሲ መኪኖች እንደተመደቡ አስታውቀዋል። ለዚህ ተግባር ደግሞ ከሚመለከታቸው አካለት ጋር ውይይት ተደርጎ መሆኑን አመላክተዋል።
ከዚህ በፊት በወልቂጤ በመናኸሪያ የነበሩ ህገ ወጥ ስራዎች በማስቀረትና እርምጃ በመውሰድ በመናኸሪያው ውስጥ አመርቂ ለውጦች ታይቷል ነው ያሉት አቶ ሙራድ።
ለአብነትም የኢቲኬቲንግ ትራንስፖርት አገልግሎት እንዲጀመር ማድረግ መቻሉና ያለአግባብ ከመናኸርያ ውጪ መጫን መቆሙ በትራንስፖርት ዘርፉ ላይ የሚቀርቡ ቅሬታዎችን መቀነስ መቻሉ ተናግረዋል።
አቶ ሙራድ አክለውም ይህ የታክሲ ትራንስፖርት ከዚህ በፊት ህዝቡ ከታሪፍ በላይ በመክፈል፣በመኪናም ሆነ በባጃጅ ውስጥ ተጨናንቆ በመሄድ ሊደርስ የሚችለው አደጋና እንግልት የሚቀርፍ መሆኑን አብራርተዋል።

የጉራጌ ዞን ትራንስፖርት እና መንገድ ልማት መምሪያ ምክትል ኃላፊ እና የትራንስፖርት ዘርፍ አስተባባሪ አቶ ግሩም ወ/ሰንበት እንዳሉት ህሙማን፣ነፍሰጡር እናቶች፣ ሽማግሌዎች እና አቅም የሌላቸው የህብረተሰብ ክፍሎች ለችግሩ የበለጠ ተጋላጭ የነበሩ ሲሆን ታክሲውም ይህንን ችግር ለመቅረፍ ታሳቢ ያደረገ መሆኑን አመላክተዋል።
በቀጣይ ደግሞ በዞኑ ባሉ ከተሞች መሰል ተግባራትና ዘመናዊ የትራንስፖርት አገልግሎቶች እንዲኖሩ ምመሪያው በትኩረት እንደሚሰራ የገለጹት አቶ ግሩም በትራንስፖርት ዘርፉ ላይ የሚስተዋሉ ችግሮችን ለማረም እና ለህብረተሰቡ ቀልጣፋ አገልግሎት ለመስጠት የሁሉም ባለድርሻ አካል ቅንጅትና ትብብር ያስፈልጋል ብለዋል።
የመምሪያው የህዝብ ትራንስፖርት አደረጃጀትና ደረጃ ብቃት ስምሪት አስተባባሪ አቶ መኮነን አመርጋ በበኩላቸው የትራንስፖርት ስምሪት ዘርፉን ለማዘመን እየተሰራ ሲሆን የኢትኬቲንግ ባልተጀመረባቸው መናኸርያዎች ተግባሩ እንዲጀምርና በትራንስፖርት ዘርፉ የተጀማመሩ ስራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ገልጸዋል።
ህብረተሰቡ በጉዞው እና በመናኸሪያ ውስጥ የተለያዩ ችግሮች ቢያጋጥሙ ስልኮች በታፔላዎች የመለጠፍ እና ታሪፍ በግልጽ ታውቆ ህዝቡ ሰላማዊ ጉዞ እንዲጓዝ እየተደረገ ነው ያሉት።

የወልቂጤ ከተማ ትራንስፖርት እና መንገድ ልማት ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ትግስቱ ተኸልቁ እንዳሉት የከተማው የትራንስፖርት አገልግሎት አሰጣጥ ለማሳለጥ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎች የሚከናወኑ ሲሆን ዛሬ ከወልቂጤ እስከ ጉብሬ ክፍለ ከተማ የተጀመረ የታክሲ አገልግሎት ተጠናክሮ እንዲቀጥል በትኩረት እንደሚሰሩ ተናግሯል።
ለዚህ ደግሞ ከማህበራቶች ጋር ውይይት ተደርጎ መወሰኑ በመግለጽ።
በወልቂጤ መናኸሪያ አግኝተን ያነጋገርናቸው ተሳፋሪዎች እንደገለጹት በከተማው ከዚ በፊት የታክሲ ትራንስፖርት አገልግሎት ባለመኖሩ ለባጃጅ እና ለመኪና ከፍተኛ ገንዘብ ይከፍሉ እንደነበር እና ዛሬ ደግሞ የታክሲ አገልግሎት መጀመሩ ደስተኞች መሆናቸው አስታውቀዋል።
በመናኸሪያው የተጀማሩ ህገ ወጥ ድርጊቶችን የማስወገድ ስራ እና ዘመናዊ የትራንስፖርት አገልግሎት አሰጣጥ ያበረታቱት ሀሳብ ሰጪዎቹ ህብረተሰቡ ደግሞ አላስፈላጊ ጭማሪዎች እንዲሁም ህገ ወጥ ድርጊቶች በመቃወም ለህግ አካል ጥቆማ መስጠት እንዳለባቸው አስታውቀዋል።
የዘገበው :-የጉራጌ ዞን መንግስት ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች መምሪያ ነው።




