የጉራጌ ማህበረሰብ ባህልና እሴት ለትዉልድ ለማስተላለፍ ሁሉም የበኩሉን መወጣት መቻል እንዳለበት የወልቂጤ ከተማ አስተዳደር ባህልና ቱሪዝም ፅህፈት ቤት አስታወቀ።

ጥር 16/2018ዓ.ም [ወልቂጤ]
በጉራጌ ዞን በወልቂጤ ከተማ አስተዳደር ነቖ (የልጃገረዶች ቀን ) በተለያየ ባህላዊ ስርዓት እና ክንውን በደማቅ ሁኔታ ተከበረ።
የወልቂጤ ከተማ አስተዳደር ባህልና ቱሪዝም ፅህፈት ቤት ሀላፊ ወ/ሪት ትእግስት ይርጋ እንደገለፁት አሁን ለአለንበት ማንነት መሰረታችን አያቶቻችን ያስቀመጡልን ባህልና ታሪክ ያለን ማህበረሰብ በመሆናችን እነዚህን እንቁ ባህሎቻችን ለትውልን ልናስተላልፍ ይገባል ሲሉ ተናግረዋል።

ትውልድ ባህሉ ጠብቆና ይዞ እንዲቀጥል የብሔሩ ተወላጆች እና በዚህ ስራ ባህል ለማሳደግ በሚደረገው ርብርብ ሁሉም አሻራውን ሊያኖር እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

የጉራጌ ማህበረሰብ ነቖ የልጃገረዶች ቀን በዓል ለሴቶች ነፃነት የሰጠበት እና ያለውን ክብር የሚያስመሰክርበት በዓል ነው ብለዋል።

ባህሉን የተሻለ ለማስተዋወቅ ትውልዱ ባህሉና ማንነት አውቆ እንዲያሳውቅ ለሌሎች እንዲያስተላልፍ በቀጣይ በሁሉም በከተማች የሚገኙ ትምህርት ቤቶች በአሉን በድምቀት እንደሚከበር ጠቁመዋል።

ትውልድ የሚገነባው በቤተሰብ በመሆኑ ወላጆች ልጆች ባህላቸውን ፣አካባቢዎች ፣ቋንቋቸውን አውቀው እንዲያድጉ የበኩላቸውን ጥረት ሊያደርጉ ይገባል ሲሉ ወ/ሪት ትዕግሥት አሳስበዋል ።

ባህላችን ለማሳደግ ከትውልድ ወደ ትውልድ ለማስተላለፍ የሁሉም ርብርብና ጥረት ከፍተኛ መሆን መቻል አለበት ያሉ ሲሆን የብሔሩ ተወላጅ ባለሀብቶች ድጋፍ ተጠናክሮ መቀጠል አለበት ብለዋል።

የበዓሉ ተሳታፊዎች በሰጡት አስተያየት በቀጣይ በተሸለ ለማክበርና በሁሉም ትምህርት ቤቶች እንዲከበርና ትውልዱ ባህሉን አውቆ እንዲያሳውቅና ከፍ ብሎ እንዲከበር ለማድረግ ርብርብ ሊደረግ ይገባል ብለዋል።

የነቖ በዓል በጥር ወር የሚከበር ሲሆን የጉራጌ ልጃገረዶች የነፃነት ቀናቸው ነው ሲሉ አንስተዋል።

በበዓሉ በወልቂጤ ከተማ አስተዳደር የሚገኙ የአንደኛና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ሴት ተማሪዎች ባህልና ስርዓቱን ተከትለው ታድመዋል።

