ህዳር O8/2O17 ዓ/ም [ወልቂጤ]
ብልጽግና ፓርቲ ከተመሰረተ ጀምሮ የተጣራ ዕሳቤን በመያዝ በሀገር ግንባታ ላይ ለውጥ ማምጣት የቻለ ፓርቲ ነው ሲሉ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ቢሮ ኃላፊ አቶ አሰፋ ደቼ ገለፁ።
”የሃሳብ ልእልና ለሁለንትናዊ ብልጽግና” በሚል መሪ ቃል የብልጽግና ፓርቲ አምስተኛ አመት ክብረ በዓልን በማስመልከት በወልቂጤ ከተማ አስተዳደር የማስ ስፖርት እንቅስቃሴ ተካሂዷል።

የብልጽግና ፓርቲ አምስተኛ አመት ምስረታን አስመልክቶ በወልቂጤ ከተማ አስተዳደር የማስ ስፖርት እንቅስቃሴ በተካሄደበት ጊዜ የተገኙት የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ቢሮ ኃላፊ አቶ አሰፋ ደቼ እንዳሉት ብልጽግና ፓርቲ በኢትዮጵያ እውነተኛ ሕብረ-ብሔራዊ ወንድማማችነት በመገንባት ለሀገሪቱ ችግር መፍትሔ የሆነው በተለይም ፓርቲው ከተመሰረተ ጊዜ ጀምሮ የጠራ ዕሳቤን በመያዝ በሀገር ግንባታ ላይ ለውጥ ማምጣት የቻለ ፓርቲ ነው ያሉ ሲሆን ለዚህም የመላ አባላቱ ሚና ከፍተኛ ነው ብለዋል።

በሀገሪቱ በማህበራዊ፣ በኢኮኖሚያዊና በፖለቲካዊ ዘርፎች ላይ የነበሩ ስብራቶችን በመጠገን በአምስት አመት ጉዞው ስኬታማ ለውጦችን ማምጣት ተችሏል ብለዋል።
እንደ ህዳሴ ግድብ የመሳሰሉ ትላልቅ የተጓተቱ ፕሮጀክቶችን እንዲጠናቀቁ ከማድረግ ባለፈ የኮሪደር ልማትና ሌሎችም የሀገር ግንባታ ላይ አስተዋጽኦ የሚያበረክቱ ስራዎች በመስራት አዎንታዊ ስኬት ማስመዝገብ እንደተቻለ የተናሩ ሲሆን በቀጣይም መላው የፓርቲው አባል መሰል ስኬቶች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ የራሱን አስተዋጽኦ ማበርከት እንዳለበትም ገልፀዋል።

የጉራጌ ዞን ምክትል አስተዳደርና የግብርና መምሪያ ኃላፊ አቶ አበራ ወንድሙ የጉራጌ ብሔር ከጥንት ጀምሮ በኢትዮጵያ ዘመናዊ ግንባታ የራሱን አስተዋጽኦ ያበረከተ ህዝብ ነው ብለው በተለይም ዝቅ ብሎ በመስራት ውጤታማ እንደሚሆን ያስተማረ ነው ሲሉም ተናግረዋል።
ብልጽግና ከተመሰረተ ወዲህ በሀገራችን በርካታ የኢኮኖሚ፣ የፖለቲካዊና የዴሞክራሲ ስራዎች እየሰራ የሚገኝ ሲሆን መሰል እሳቤዎችና ሌሎችም ዘርፎች ላይ ብልጽግናን ለማረጋገጥ ከመላው ህዝብና አመራሩ ጋር በቅንጅት የሚሰራው ስራ ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።
ሕብረ-ብሔራዊ ወንድማማችነትን ለማጠናከር በርካታ ስራዎች እየተሰሩ መሆኑን ጠቁመው የሽግግር ፍትህና ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ማሳያ እንደሆኑም ገልጸዋል።
በመሆኑም ሠላም የሁሉም ነገር መሰረት መሆኑና አሁን ላይ በዞኑ ያለውን አንፃራዊ ሠላም ተጠናክሮ እንዲቀጥል መላው አባላት ከመንግሥት ጎን በመሆን ድጋፍ ማድረግ ይጠበቅባችኋል ነው ያሉት።

የወልቂጤ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ሙራድ ከድር በበኩላቸው ፓርቲው በአምስት አመታት ውስጥ በርካታ የተፈጥሮና ሠው ሠራሽ ችግሮችን በመጋፈጥ ስኬት ማስመዝገብ የቻለ መሆኑን ገልፀዋል።
የፖለቲካ ብልጽግናን ለማምጣት በርካታ ማሻሻያዎችን አድርጎ በሀገሪቱ የሚገኝ ሁሉም ዜጋ በእኩል እንዲሳተፍ ያደረገ ፓርቲ ነው ያሉት አቶ ሙራድ የኢኮኖሚ ብልጽግና እንዲመጣ በተሰራው ስራም የሚጨበጡ ለውጦች ማምጣት ተችሏል ብለዋል።
ፕሮጀክቶችን ጀምሮ መጨረስ ባህሉን ያደረገው ፓርቲው እንደ ገበታ ለሃገርና ሌሎችም አዳዲስ ፕሮጀክቶች በመገንባት ትውልድ ተሻጋሪ ስራዎች እየሰራ ይገኛል ብለዋል።
እንደ አቶ ሙራድ ገለፃ ቀደም ባሉ ጊዜያት በኢትዮጵያ የነበሩ አሳሪ ህጎችን ሪፎርም በማድረግና በማሻሻል ለውጥ እንዲመጣ ያስቻለ ሲሆን በውጭ ግንኙነት በተሰሩ የዲፕሎማሲያዊ ስራዎች የኖቤል ተሸላሚ ከመሆን ጀምሮ የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ተስፋ የፈነጠቀበትና እምርታዊ ለውጥ ማምጣት የተቻለበት ነው።

ባለፉት አምስት አመታት ፓርቲው ባስመዘገባቸው ስኬቶች እንዲሁም በገጠሙት ፈተናዎች በመቋቋም ፓርቲውን ለማፅናት የከተማው ማህበረሰብና ወጣቶች ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማበርከታቸውንና ለዚህም ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
በመሆኑም በከተማው በሁሉም ዘርፍ ብልጽግናን ለማምጣት ሠላም ወሳኝ እንደሆነ በተለይም በተለይም የህግ የበላይነትን ለማረጋገጥ ሠላምን ለማስፈን በሚደረገው እንቅስቃሴ ሁሉም መደገፍ እንዳለበትም አቶ ሙራድ መልእክት አስተላልፈዋል።

በማስ ስፖርት እንቅስቃሴው ላይ የተሳተፉ አባላት እንዳሉት ስፖርት ጤንነትን ከማጎልበት ባለፈ አንድነትን የሚያጠናክር መሆኑን ተናግረው ቀጣይም ፓርቲው የያዛቸውን ዕቅዶች ከግብ እንዲደርሱ የድርሻቸውን እንደሚወጡም ተናግረዋል።

በመርሃ-ግብሩ ላይ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ቢሮ ኃላፊ አቶ አሰፋ ደቼ፣ የጉራጌ ዞን ምክትል አስተዳዳሪ አቶ አበራ ወንድሙ፣ የዞኑ ዋና የመንግሥት ተጠሪ አቶ አለማየሁ ገብረ መስቀልና የወልቂጤ ከተማ ከንቲባ አቶ ሙራድ ከድር፣ የወልቂጤ ከተማ አስተዳደር ብልጽግና ፓርት ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ታደለ በቀለን ጨምሮ ከዞንና ከወልቂጤ ከተማ የተውጣጡ አመራሮች፣ ነዋሪዎች እና ሌሎችም ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል።

