ህዳር O7/2O17 ዓ/ም [ወልቂጤ]
ከተማው በሁለንተናዊ የልማት ዘርፎች ላይ ለማሳደግ የሚደረገውን እንቅስቃሴ በመደገፍ ረገድ የወጣቶች ሚና የጎላ መሆን እንዳለበት የወልቂጤ ከተማ አስተዳደር አስታወቀ።
ከተማ አስተዳደሩ በከተማው በሚሰሩ የልማት ስራዎች ላይ ያተኮረ ውይይት ከወጣቶች ጋር አካሂዷል።

የወልቂጤ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ሙራድ ከድር በከተማው በሚሰሩ የልማት ስራዎች ላይ ያተኮረ ውይይት ከወጣቶች ጋር በተካሄደበት ወቅት እንደተናገሩት ከተማው የብዙ ፀጋዎች መገኛ ቢሆንም በሚፈለገው ልክ ዕድገት አላሳየም።
የከተማውን ዕድገት ከፍ ሊያደርጉ የሚችሉ በርካታ ዕድሎች እንዳሉ የተናገሩት አቶ ሙራድ በተለይም እነዚህን ዕድሎችን በመጠቀም ከተማ አስተዳደሩ በሁለንተናዊ የልማት ዘርፎች ላይ ለማሳደግ የሚደረገው እንቅስቃሴ በመደገፍ ረገድ የወጣቶች ሚና የጎላ መሆን እንዳለበትም አስረድተዋል።
አመራሩ ለከተማው ዕድገት መፋጠን ያሉን ሁሉ ዕድሎችን ተጠቅሞ በቁርጠኝነት እንደሚሰራ ገልፀው በዋናነት የሚሰሩትን የልማትና መልካም አስተዳደር ስራዎች ከግብ እንዲደርሱ ሁሉም የድርሻውን ሊወጣ ይገባልም ብለዋል።

የንግድ ቀጠና፣ የምሁራን መፍለቂያና የበርካታ እንግዶች መንቀሳቀሻ የሆነው ወልቂጤ ከተማ የሚመጥነውን የዕድገት ደረጃ ለማድረስ ወጣቱ ተሳትፎውን ማጎልበት ይጠበቅበታል ነው ያሉት።
በዋናነት ወጣቱ የሠላም አምባሳደር በመሆን ችግሮች ካሉ ተቀራርቦ በመነጋገርና አፍራሽ የሆኑ የማህበራዊ ሚዲያ አጠቃቀሞችን በመታገል እንዲሁም ህገ-ወጥ የመሬት ወረራን በመከላከልና በሌሎችም ዘርፎች የበኩሉን እንዲወጣ አስገንዝበዋል።
በተያዘው በጀት ዓመት በከተማው ከአንድ ቢሊዮን ብር በላይ ለመሰብሰብ መታቀዱን ጠቁመው ዕቅዱ እንዲሳካ የሁሉም እርብርብ ይጠይቃል ብለዋል።

የከተማው መንግሥትም የሚሰሩ ስራዎች ወጣቱን ባሳተፈ መልኩ ይሰራል በማለት በተለይ በፍትሐዊነት የስራ ዕድል እንዲፈጠርና ከወጣቶች መዝናኛ ጋር ያሉ ውስንነቶች እንዲቀረፍ ይደረጋል ብለዋል።
ወልቂጤ የሁሉም ብሔር-ብሔረሰብ መኖሪያ እንደመሆኗ ሠላሟን እንዲጠበቅ በማድረጉ ላይም ወጣቱ ከፀጥታው አካል ጋር ተቀናጅቶ መስራት ይጠበቅበታል ሲሉም አሳስበዋል።
የመወያያ ሠነዱን ያቀረቡት የወልቂጤ ከተማ አስተዳደር ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ታደለ በቀለ ሀገሪቱ በተለያዩ ችግሮች ላይ ሆና በማህበራዊ፣ በኢኮኖሚያዊ፣ በፖለቲካዊና በሌሎችም ዘርፎች ላስመዘገበችው ስኬት የወጣቱ ሚና ጉልህ እንደነበር ገልፀዋል።

ብልጽግና ፓርቲ አሁን ላመጣው ስርዓት የወጣቱ ሚና ከፍተኛ ነው ብሎ ያምናል ያሉት አቶ ታደለ እንደ ከተማ አስተዳደሩም ሆነ እንደ ሀገር ብልጽግና ፓርቲ ሊያሳካቸው ያቀዳቸውን ዕቅዶች ከግብ እንዲደርሱ ወጣቱ የጀመረውን ተሳትፎ አጠናክሮ ማስቀጠል ይኖርበታል ብለዋል።
በከተማ አስተዳደሩ ዕድገት ለማምጣት ከከተማው ማህበረሰብ ጋር በአደረጃጀቶች የታገዘ ውይይት እንደሚደረግ ገልፀው በውይይቱ የተነሱ ውስንነቶችን በመቅረፍ ጠንካራ ጎኖች እንዲቀጥሉ ይደረጋል ሲሉም ጠቁመዋል።
በከተማ አስተዳደሩ ለመገንባት የታቀደው የኮሪደር ልማትም ውጤታማ እንዲሆን ምቹ ሁኔታዎችን በመፍጠሩ ረገድ ወጣቶች ጨምሮ ከከተማው ነዋሪ ይጠበቃል ብለዋል።

ህገ-ወጥ አሰራሮችን በመታገል ከተማው ወደ ተሻለ ዕድገት እንዲሸጋገር ተጋግዞና ተቀናጅቶ መስራት ወሳኝ ስለመሆኑ አንስተው ወጣቱም በተግባር ማሳየት ይጠበቅበታል በማለት አጽንኦት ሰጥተዋል።
እንደ ከተማ አስተዳደሩ በወጣቶች ስብዕና ግንባታ ላይ ትኩረት ተሰጥቶ እንደሚሰራም ተናግረዋል።
የውይይቱ ተሳታፊ ወጣቶች በበኩላቸው ወጣቱ ከመንግሥት ጋር በመቀናጀት ለከተማው ለውጥ ይሰራል ብለዋል።
በከተማው የተጀመሩ የልማትና መልካም አስተዳደር ስራዎችን ለማሳለጥ ጠንካራ የገቢ አሰባሰብ ስራ ሊሰራ እንደሚገባም ገልፀዋል።
ለወጣቱ በቂ የስራ ዕድል ከመፍጠር አኳያ፣ ከባለሃብቱ ጋር ተቀራርቦ ከመስራት አንፃር፣ በባጃጅ የሚፈፀሙ የስርቆት ወንጀሎች፣ የወጣቶች መዋያ ቦታ፣ በከተማው የህግ የበላይነት ከማስከበር አንፃርና ሌሎችም ሀሳቦችና ጥያቄዎች ከወጣቶቹ የተነሱ ሲሆን ከመድረኩ ምላሽና ማብራሪያ ተሰጥቶባቸዋል።

