ግንቦት 19/2O16 ዓ/ም [ወልቂጤ]
የገቢ አቅም አሟጦ ለመሰብሰብ በሚደረገው እንቅስቃሴ ሁሉም ባለድርሻ አካል በቅንጅት ሊሰራ እንደሚገባ የወልቂጤ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ እንዳለ ስጦታው ገለፁ።
የከተማው ገቢ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት በቀሪ ወራት ገቢን አሟጦ መሰበሰብ በሚቻልባቸው ጉዳዮች ላይ ከባለድርሻ አካላት ጋር የውይይት መድረክ አካሂዷል፡፡

የወልቂጤ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ እንዳለ ስጦታው በውይይት መድረኩ እንደገለፁት የከተማው ኢኮኖሚ የሚያመነጨው ገቢ አሟጦ ለመሰብሰብ በሚደረገው እንቅስቃሴ ሁሉም ባለድርሻ አካል በቅንጅት ሊሰራ እንደሚገባ ተናግረዋል።
በቀሪ ወራት ገቢን አሟጦ መሰበሰብ ያስፈልጋል ያሉት ከንቲባው በዚህም አመራሩ የገቢ ሴክተርን በተገቢው ሊደግፍ እንደሚገባም ነው የጠቆሙት፡፡
ከግብር ከፋዮች የተጣለባቸው የዘመኑን ግብር በወቅቱና በታማኝነት እንዲከፈል ከማድረግ ጎን ለጎንም የንግድ ስራ ፈቃድ እድሳት እንዲጠናቀቅ ማድረግ እንደሚገባም ገልፀዋል።

የከተማው ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አብድልበር ሰይድ በበኩላቸው ግብር በአንድ ሃገር ወሳኝ የሆነ የመሰረተ ልማት ፍላጎትን ለማሟላት ጉልህ ሚና ይጫወታል።

በዚህም መንግሥት የገቢ አሰባሰብ ስርዓቱን ከኪራይ ሰብሳቢነት የፀዳ ለማድረግ በየጊዜው የታክስ ፖሊሲና ህጎችን በማውጣት በሚያከናውናቸው ዘርፈ ብዙ ጥረቶች ለውጦች እየታዩ መሆኑንም ጠቁመዋል።
በከተማው በየደረጃው የተጀመሩ የልማት ተግባራት ከዳር ለማድረስ የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ግብር ከፋዩ ግብርን በወቅቱ መክፈል እንዳለበት ተናግረው ለተፈፃሚነቱም ሁሉም የድርሻውን ሊወጣ እንደሚገባም አሳስበዋል።

የከተማ አስተዳደሩ ገቢዎች ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አብድልከሪም መሐመድ በዚሁ ወቅት እንዳሉት በየጊዜው እያደገ የመጣውን የህብረተሰቡን የልማትና መልካም አስተዳደር ጥያቄ ለመመለስ የታክስ አሰባሰቡ ሂደት ላይ በትኩረት እየተሰራ ነው ብለዋል።

በ2O16 በጀት አመት ከመደበኛና ማዘጋጃ ቤታዊ አገልግሎት ለመሰብሰብ ከታቀደው እቅድ አንጻር አሁን ላይ የተሻለ ደረጃ ላይ እንደሚገኝ የተናገሩት ሃላፊው ይሁንጂ እቅዱን መሉ በሙሉ ለማሳካት በበጀት አመቱ ባሉት ቀሪ ወራት በቅንጅት መስራት ይገባል ብለዋል።

በመድረኩም በቀሪ ወራት ገቢን አሟጦ መሰበሰብ በሚቻልባቸው ጉዳዮችን አስመልክቶ ለተነሱ ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ ከመድረኩ የተሰጠ ሲሆን አመራሮቹም የተጣለባቸውን ኃላፊነት በትጋትና በቁርጠኝነት ለመወጣት መዘጋጀታቸውንም ጠቁመዋል፡፡

