የሆቴል ኢንቨስትመንት ቱሪስቶችን ከመሳብ ባለፈ ለዜጎች የሚፈጥረው የስራ እድል ከፍተኛ በመሆኑ ዘርፉን ለማሳደግ በትኩረት ሊሰራ እንደሚገባ ተገለጸ።
የካቲት16/2016ዓ.ም
============== የሆቴል ኢንቨስትመንት ቱሪስቶችን ከመሳብ ባለፈ ለዜጎች የሚፈጥረው የስራ እድል ከፍተኛ በመሆኑ ዘርፉን ለማሳደግ በትኩረት ሊሰራ እንደሚገባ ተገለጸ።

በወልቂጤ ከተማ ከ500 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ የተገነባው ፍፁም በላይ ሆቴል ተመርቆ አገልግሎት መስጠት ጀመረ።
የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ምክርቤት ዋና አፈጉባኤ ክብርት ወይዘሮ ፋጤ ሰርሞሎ በፍፁም በላይ ሆቴል የምረቃ ስነ ስርዓት ላይ ተገኝተው ባደረጉት ንግግር ጉራጌ ጠንካራ የስራ ባህል ያለው ከአካባቢው አልፎ በሌሎች የሀገሪቱ ክፍሎች መዋዕለ ነዋዩን በማፍሰስ ልማትን በማፋጠንና ሀገር በማቅናት ረገድ እያደረገ ያለው አስተዋጽኦ ከፍተኛ ነው ብለዋል።

በሆቴል ኢንቨስትመንት ዘርፍ በመሰማራት ውጤታማ ከሆኑ ባለሀብቶች መካከል ቀኝ አዝማች በላይ ኬርስማ ተጠቃሽ ሲሆኑ ባለሀብቱ ያስገነቡት ፍፁም በላይ ሆቴል ከኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታው ባለፈ በከተማው ለሚገኙ ስራ አጥ ዜጎች የስራ እድል እንዲፈጠርላቸው ያስችላል ብለዋል ክብርት አፈጉባኤዋ።
ባለሀብቱ በወልቂጤ ከተማ የሚስተዋለው የውሃ ችግር ለመቋቋም የከርሰ ምድር ውሃ በማስቆፈር ከሆቴሉ ባለፈ ያካባቢው ማህበረሰብ የውሃ ችግር ማቃለል መቻላቸውን እንዳስደሰታቸው ገልጸዋል።
በመሆኑም ወልቂጤ ከተማ ለማሳደግ ሌሎች ባለሀብቶች ተሳትፏቸው ማጠናከር ይገባል ያሉት ክብርት አፈጉባኤዋ የከተማው አስተዳደር ባለሀብቶች ለመሳብ የኢንቨስትመንት ቦታዎች አዘጋጅቶ መጋበዝ አለበት ብለዋል።
የክልሉ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ አቶ ሳሙኤል መንገሻ በበኩላቸው በክልሉ የሆቴል ኢንዱስትሪ እየተስፋፋ ከሚገኝባቸው አካባቢዎች አንዱ ወልቂጤ ከተማ ሲሆን ምዕራብ ኢትዮጵያ የቱሪዝም እንቅስቃሴ እንዲፋጠን ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያበረክታል ብለዋል።

እንደ ኃላፊው ገለፃ ለምርቃት የበቃው ፍፁም በላይ ሆቴል የከተማው የቱሪስት አገልግሎት አሰጣጥ ጥራት ያሻሽላል።
የጉራጌ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ላጫ ጋሩማ በበኩላቸው ቀኝ አዝማች በላይ ኬርስማ እጅግ ቅንጡ፣ ውብና ደረጃውን የጠበቀ እንዲሁም በከተማው ከተገነቡ ሆቴሎች የተሻለ ደረጃ ያሰጠዋል ብለዋል።
እንደ አቶ ላጫ ገለጻ የሆቴሉ ጥራትና ደረጃ የወልቂጤ ከተማ ገጽታን የሚለውጥና ከሀገር መሪዎች ጀምሮ ሌሎችም እንግዶች በኩራት ለማስተናገድ ያስችላል።

የወልቂጤ ከተማ ከንቲባ አቶ እንዳለ ስጦታው እንደተናገሩት ሆቴሉ የከተማው የውሃ ችግር ለማቃለል ከ10 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ የከርሰ ምድር ውሃ በማስቆፈር ለሌሎች ባለሀብቶች በምሳሌነት የሚጠቀስ ኢንቨስትመንት ነው።
ወልቂጤ ከተማ የምዕራብ ኢትዮጵያ የልማት ኮሪደር በመሆኗ በቀጣይ የሆቴል ኢንዱስትሪ ለማስፋፋት የሚያስችሉ ተግባራት እየተከናወኑ ሲሆኑ ሌሎች ባለሀብቶች በከተማው መዋዕለንዋያቸውን እንዲያፈሱ ጥሪ አቅርበዋል።

የፍጹም በላይ ሆቴል ባለቤት ቀኝ አዝማች በላይ ኬርስማ ሆቴሉ 10 የልዩ እንግዳ ጨምሮ ደረጃቸውን የጠበቁ 50 ማረፊያዎች፣ ለባንክ እና ለልዩ ልዩ የንግድ አገልግሎት የሚውሉ ክፍሎች ያሉት ሲሆን የባርና የሬስቶራንት አገልግሎት ይሰጣል ብለዋል።

ለሆቴሉ ግንባታ ከ500 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ መደረጉንም ቀኝ አዝማች በላይ ገልጸዋል።
ሆቴሉ እጅግ ዘመናዊና የጉራጌን ባህል የጠበቀ ሲሆን ለ85 ዜጎች የስራ እድል መፍጠር መቻሉ ገልጸዋል።
በሆቴሉ 24 ሰዓት ሙሉ ውሃ የማይጠፋበት ብቻ ሳይሆን ጥራት ያለው ቀልጣፋ አገልግሎት እንደሚሰጥ ተናግረዋል።



