“ህብረ ብሔራዊ ወንድማማችነት ለዘላቂ ሠላም እና ሁለንተናዊ ብልፅግና” በሚል መሪ ሀሳብ የተዘጋጀ የውይይት መድረክ በወልቂጤ ከተማ እየተካሄደ ነው።
የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አረጋ ከበደ በመድረኩ ተገኝተው ባስተላለፉት መልዕከት የውይይት መድረኩ በሀገሪቱ በ20 ከተሞች እየተደረገ መሆኑን ጠቅሰው በመድረኩ የሚነሳውን የህዝቡን ሀሳብ ወስደን የቀጣይ እቅድ አካል በማድረግ እንሠራለን ብለዋል።

በውይይት መድረኩ ላይ የሀገሪቱና የአካባቢው አጠቃላይ የሰላም፣ የልማት እና መልካም አስተዳደር እንዲሁም የሀገሪቱ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ጉዳይ ጭምር ያለበት ሁኔታ ምን እንደሚመስል ውይይት የሚደረግ ስለመሆኑም አንስተዋል።
በውይይት መርሃ ግብሩ ላይ የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አረጋ ከበደ፣ የብልጽግና ፓርቲ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባልና የሲዳማ ክልል ዋና የመንግስት ተጠሪ አቶ አብርሃም ማርሻሎ፣ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ረዳት የመንግስት ተጠሪ አቶ ይግለጡ አብዛ እና የጉራጌ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ላጫ ጋሩማን ጨምሮ የዞንና የከተማው አመራሮች እና የአካባቢው ነዋሪዎች እንዲሁም ሌሎች ተጋባዥ እንግዶች ተሳትፈዋል።


