
የጉራጌ ብሄር ከጥንት ጀምሮ የሚተዳደርበት ባህላዊ የአስተዳደር ስርአት እና ጠንካራ ባህላዊ እሴት ያለው ማህበረሰብ ነው።
ይህ የብሄሩ መተዳደሪያ ባህላዊ አስዳደር ስርአት በተለያዩ ስሞች ሲጠራ የቆየ ሲሆን እነሱም የጆካ ቂጫ(የሰባት ቤት ጉራጌ)፣የሶዶ ጎርደና ሴራ(የክስታኔ ጉራጌ)፣የጎርዳና ሴራ (የገ/ጉ/ወ ቤተ ጉራጌ)፣የፈራገዘኘ ሴራ(የመስቃን ቤተ ጉራጌ) እና የዶቤ ጎጎት ስናኖ ሴራ(የዶቢ ቤተ ጉራጌ)ባህላዊ አስተዳደር ስርአቶች ናቸው።

እንደዞን አንድ የጋራና ሁሉም ሊያግባባ በሚችል የባህል ሸንጎ መመስረት የሚያስችል የዳሰሳ ጥናት የሚያደርግ ከተለያዩ አካላት ማለትም ከዞን አስተዳደር፣ከባህል ቱሪዝም መምሪያ፣ከወልቂጤ ዩኒቨርስቲ ፣ከአቃቤያን ህግ፣ ከፍትህ መምሪያ፣ ከጉልባማ እና ከሌሎች ተቋማት የተወጣጡ የጥናት ቡድን ቋቁሞና ጥናት ተደርጎ ጥናቱን መሰረት በማድረግ የጉራጌ ሸንጎ በቡታጅራ ከተማ በ2013 ዓ.ም ተመስርቶ ስራውን ጀመረ።
የባህላዊ ሸንጎው ወቅቱን ከሚጠይቀው አጠቃላይ ሁኔታዎች አንጻር የብሄሩን፣የዞኑንና የሀገር አንድነት ላይ ሊኖረው የሚገባ ትልቅ ሚና ከፍ በማድረግ በተሻለ አደረጃጀት ይዘቱንና ትውፊቱን ጠብቆ መምራት እጅግ ጠቃሚና ከትውልድ ወደ ትውልድ ለማሸጋገር ያለው ሚና ከፍተኛ ነው።

ይህ ጉባኤም የጉራጌ ሰላምና አንድነት፣ልማትና አብሮነትን ለማጠናከር በሌሎች ጉዳዮች ላይ የጋራ መግባባት ይፈጥራል ተብሎ ይጠበቃል።
በመድረኩም የጉራጌ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ላጫ ጋሩማ፣የምስራቅ ጉራጌ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ሙስጠፉ ሀሰን፣የጉራጌ ዞን ዋና አፈ ጉባኤ ክብርት ወ/ሮ ልክነሽ ስርግማ፣የምስራቅ ጉራጌ ዞን ዋና አፈ ጉባኤ አቶ እንዳልካቸው ጌታቸው የጉራጌ ዞን ባህል ቱሪዝም መምሪያ ወ/ሮ መሰረት አመርጋ፣የምስራቅ ጉራጌ ዞን ባህል ቱሪዝም መምሪያ ኃላፊ ወ/ሮ ብሩክታዊት ጸጋዬ የጉልባማ ስራ አስከያጅ አቶ ቅባቱ ተሰማ፣የጉራጌ የባህል ሸንጎ ምክትል ሰብሳቢ አዝማች ጸጋዬ ታቦር ጨምሮ ከሁለቱም ዞኖች የተወጣጡ የባህል ሽማግሌዎች ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።

