መንግስት በወልቂጤ ከተማ የተፈጠረው የጸጥታ ችግር በዘላቂነት እንዲቀረፍ የህግ የበላይነት ማስፈን እንዳለበት የከተማው የሀገር ሽማግሌዎች ጠየቁ።
በወልቂጤ ከተማ እየተፈጠረ ያለው የጸጥታ ችግር ለመፍታት ከከተማው ሽማግሌዎች ጋር ውይይት ተደርጓል።
በከተማው እየፈጠረ ያለው የጸጥታ ችግር ለመፍታት በሚደረገው ጥረት የሀገር ሽማግሌዎች ሚናቸው የጎላ መሆኑን ተገለጸ።
በውይይት መድረኩ የተሳተፉ የከተማው የሀገር ሽማግሌዎች እንዳሉት መንግስት በከተማው እየተፈጠሩ ያሉ ችግሮችን በዘላቂነት ለመቅረፍ፣ የህግ የበላይነት እንዲከበር በትኩረት መስራት እንደሚጠበቅበት ገልጸዋል። ለዚህም ማህበረሰቡ በሚወስዳቸው ህግ የማስከበር ስራዎች ከመንግስት ጎን በመቆም እንደሚያግዙ ተናግረዋል።
የወልቂጤ ከተማ አስተዳደር ወሰን እንዲከበር የከተማው ማህበረሰብ ለአመታት ሲጠይቅ እንደነበር የተናገሩት ተሳታፊዎቹ ጥያቄው በወቅቱ ምላሽ ባለማግኘቱ ለግጭቱ መንስኤ እንዲሆን አስችሎታል ብለዋል።
ህዝብ ከህዝብ በማጋጨት የራሳቸው ኪስ የሚያደልቡ የመሬት ደላሎችና ኮንትሮባንዲስቶች የማህበራዊ ሚዲያ በመጠቀም በህዝቡ መካከል አለመተማመንና ጥርጣሬ እንዲሰፍን የሚያደርጉ አካላት ላይ መንግስት ህጋዊ እርምጃ ሊወስድ ይገባል ነው ያሉት።
በከተማዋ ሰላማዊና እንቅስቃሴ እንዳይኖር የንብረት ዝርፊያ ፣ ውድመት፣ ቤተሰብ ማፈናቀልና የግድያ ወንጀል የፈጸሙ አካላት ተገቢውን እርምጃ ሊወሰድባቸው እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
በተጨማሪም ህጻናት ከትምህርት ገበታቸው እንዲርቁ ትምህርት ቤቶች የሚያዘጉና የመንግስት ተቋማት አገልግሎት እንዳይሰጡ የሚያደናቅፉ አካላት ተጠያቂ ለማድረግ መንግስት ትኩረት ሰጥቶ ሊሰራበት ይገባል ብለዋል።
በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የትራንስፖርትና መንገድ ልማት ቢሮ ኃላፊ ዶክተር መሀመድ ኑሪዬ መድረኩ በመሩበት ወቅት እንዳሉት የከተማው ህዝብ በሰላም ወጥቶ እንዳይገባ ህዝብ ከህዝብ በሚያጋጩ ጸረ ሰላም ሀይሎች ላይ ህጋዊ እርምጃ እንደሚወሰድ ተናግረዋል።
የህግ የበላይነት ለማስከበር በሚደረገው ጥረት ህብረተሰቡ ከጸጥታ ሀይሉ ጎን በመሆን ሊያግዝ እንደሚገባ አንስተዋል። በዚህም የሀገር ሽማግሌዎች ሚናቸው የጎላ ነው ብለዋል።
የወልቂጤ ከተማ አስተዳደር ወሰን የማስከበር ጉዳይ የህብረተሰቡ የቆየ ጥያቄ ቢሆንም ጥያቄው ምላሽ እንዲያገኝ የክልሉ መንግስት በህግ አግባብ እንደሚፈታው ገልጸዋል።

የከተማው ሰላም ለማደፍረስ የሚንቀሳቀሱ ግለሰቦች ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ የአካባቢው ሽማግሌዎች ልጆቻቸውን መገሰጽና መምከር አለባቸው ያሉት ዶክተር መሀመድ ከዚህም ባለፈ ህዝቡን በሰላም ወጥቶ እንዳይገባ የሚያደርጉ አካላትን ለህግ አሳልፈው እንዲሰጡም ጠይቀዋል።
የከተማው ሰላም ለማረጋገጥ የክልሉ መንግስት በትኩረት እንደሚሰራ አመላክተው ለዚህም የሀገር ሽማግሌዎችና የሀይማኖት አባቶች ከመንግስት ጎን በመሆን ማገዝ ይኖርባችኋል።
በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የመንግስት ረዳት ተጠሪ አቶ ይግለጡ አብዛ በበኩላቸው በከተማው የተፈጠረው የጸጥታ ችግር ለመፍታት በርካታ ስራዎች እየተሰራ እንደሚገኝ ጠቅሰው በዚህም የህግ የበላይነት የማስከበሩ ስራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል።
ማህበራዊ ሚዲያዎች በመጠቀም ህዝብ ከህዝብ፣ ብሔር ከብሔር በማጋጨት የግል ኪሳቸውን የሚያደልቡ አካላት መኖራቸውን አመላክተው በእነዚህ ወንጀለኞች ላይ ህጋዊ እርምጃ እንደሚወሰድ ተናግረዋል።
የወልቂጤ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ እንዳለ ስጦታው የከተማዋ ማህበረሰብ ለዘመናት የመልማት ጥያቄዎች እንዲመለሱ ለመንግስት በርካታ ጥያቄዎች ሲያነሳ ቢቆይም ጥያቄው መንግስት በህግና በአሰራር መሰረት እመልሳለሁ በማለቱ ማህበረሰቡ በትዕግስት እየተጠባበቀ ይገኛል።
ከነዚህም አንዱ የከተማው የአስተዳደር ወሰን እንዲከበር ሲጠየቅ መቆየታቸውና ያደረ የዘመናት ጥያቄ መሆኑን አንስተው ይህም ከክልሉ መንግስት ጋር በመሆን በህግና አሰራር መሰረት ለመፍታት እንደሚሰራ ተናግረዋል።
ከተማው በርካታ ብሔር ብሔረሰብች በአብሮነት የሚኖሩባት ከተማ መሆኗን ያነሱት ከንቲባው በተሳሳተ ትርክት ህብረተሰቡ በሰላም እንዳይኖር ግጭት የሚፈጥሩ አካላት አይሳካላቸውም ብለዋል።
የከተማው ህዝብ ከልማት ለመነጠል የሚደረጉ ህገ ወጥ ተግባራት ማህበረሰቡ በመረዳት ህገወጦችን አሳልፎ ለመስጠት የአካባቢው ሽማግሌዎች እገዛ እንዲያደርጉ ጠይቀዋል


