የከተማውን የልማትና የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለመቅረፍ በትኩረት እንደሚሰራ የወልቂጤ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ እንዳለ ስጦታው አስታወቁ።

መስከረም 23/2O16 ዓ/ም [ወልቂጤ]

የከተማውን የልማትና የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለመቅረፍ በትኩረት እንደሚሰራ የወልቂጤ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ እንዳለ ስጦታው አስታወቁ።

ከንቲባው ይህን ያሉት የከተማ አስተዳደሩ ምክር ቤት 2ኛ ዙር 11ኛ አመት 38ኛው መደበኛ ጉባዔ በካሄደበት ወቅት ነው።

ምክር ቤቱ ለ2O16 የስራ ዘመን ከ6 መቶ 2O ሚሊዮን ብር በላይ በጀት አጽድቋል፡፡

የወልቂጤ ከተማ አስተዳደር ምክር ቤት 2ኛ ዙር 11ኛ አመት 3Oኛ መደበኛ ጉባዔ ያካሄደ ሲሆን በጉባዔውም በከተማው በተለያዩ የልማት ዘርፎች የተሰሩ ስራዎች ገምግሟል።

የከተማ አስተዳደሩ ከንቲባ አቶ እንዳለ ስጦታው በዚህ ወቅት እንዳሉት የከተማው የልማትና የመልካም አስተዳደር ችግሮችን በመቅረፍ በቀጣይ ከተማዋ መድረስ ያለባት ደረጃ እንድትደርስ በትኩረት ይሰራል ብለዋል።

የከተማው ማህበረሰብ የልማት ጥማት አለበት ያሉት ከንቲባው በተለይም የተመደበ በጀትን በተገቢው ከማዋል ባለፈ አመራሩ መርህን ተከትሎ በመስራት ይህንኑ በውጤታማነት ያሳያል ሲሉም ገልፀዋል።

በከተማ አስተዳደሩ በርካታ ያደሩ የልማት ስራዎች መኖራቸውን ጠቅሰው እነዚህም ደረጃ በደረጃ ለመፍታት የተጠናከረ ስራ እንደሚሰራ ተናግረው በተለይ የንፁህ መጠጥ ውሃ ስርጭት ችግር ለመቅረፍ በተሰራው ስራ ውጤት መኖሩን አመላክተዋል።

ችግሩን በዘላቂነት ለመቅረፍም የጣጤሳ ጥልቅ የውሃ ጉድጓድ ስራ ለማስጀመር ሁለት ትራንስፎርመር እንዲገባ ከማድረግ ባለፈ ከኢፌዴሪ ውሃ ሚኒስቴር ጋር በመተባበር ከ26 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት የውሃ መሳሪያ ማስገባት ተችሏል ብለዋል።

በመንገድ መሰረተ ልማት ላይም ሰፊ ስራ እየተሰራ መሆኑን ጠቁመው ይህም ለከተማው እድገት ፋይዳው የጎላ በመሆኑ ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል ከንቲባው።

በከተማው ህገ-ወጥ ግንባታን በመከላከሉ ላይ አበረታች ስራ መሰራቱንና በህገ-ወጥ የተያዙ ቦታዎችን የመለየት ስራ መሰራቱን ገልፀው በቀጣይም በዘርፉ ውጤት ለማምጣት አመራሩ በቁርጠኝነት እንደሚሰራም ተናግረዋል።

በከተማው የግብርናውን ዘርፍ በማጠናከር ሌሎች አማራጮችን በመጠቀም ማህበረሰቡ እየተቸገረ ያለበትን የኑሮ ውድነት ለማቅለል የተጀመሩ ስራዎች ተጠናክረው ይቀጥላሉ ሲሉም አስረድተዋል።

ለወጣቶች የስራ ዕድል ለመፍጠር ትኩረት ይደረጋል በማለት ባለፉት ጊዜያት ለኢንተርፕራይዞች የተላለፉ ሼዶች እንዲመለሱ ማድረግ ተገቢ እንደሆነም ነው የገለፁት።

በከተማ አስተዳደሩ በጤናውና በትምህርቱ ዘርፍ ላይ ያሉ ስኬታማ ስራዎች ማስቀጠል ተገቢ መሆኑን የተናገሩት ከንቲባው ለዚህም ህዝቡ አጋዥ ሊሆን እንደሚገባም አመላክተዋል።

ለዚህም ደግሞ ገቢን በተገቢው በመሰብሰብ ለታለመለት ዓላማ ማዋል ከአመራሩ ይጠበቃል ብለዋል።

ከተማው በ1996 ዓመተ ምህረት የፀደቀው ፕላን ያለው መሆኑና ከዛ ውጪ ያሉት ማህበረሰቡን ብዥታ ውስጥ ለመክተት ነው ብለዋል።

የከተማ አስተዳደሩ ምክር ቤት ዋና አፈ-ጉባዔ አቶ ሸምሱ በሽር እንደገለጹት ምክር ቤቶች የህዝብ ሉዓላዊ መገለጫዎች በመሆናቸው የምክር ቤቱ አባላት ለተወከሉበት ማህበረሰብ በርካታ የልማት ጥያቄዎች ምላሽ እንዲያገኙ በማድረግና የዴሞክራሲ ስርዓቱን ለማጠናከር እየሰራ ይገኛል ብለዋል፡፡

ህብረተሰቡ በሁለንተናዊ ልማትተጠቃሚ ለማድረግ የምክር ቤት አባላት በተደራጀና በተጠናከረ መልኩ መስራት እንዳለባቸው አቶ ሸምሱ አሳስበዋል፡፡

ተጀምረው ያልተጠናቀቁ ፕሮጀክቶች ማጠናቀቅ፣ የኑሮ ውድነት ችግር መቅረፍ፣ የተሰበሰበ ገቢ ለታለመለት ዓላማ ማዋል፣ ፍትሃዊ የሃብት ክፍፍል፣ ለወጣቶች የተሰራጨ ብድር ማስመለስ፣ የከተማው ሳምንታዊ ገበያ ማጠናከርና ሌሎችም አስተያየቶችና ጥያቄዎች ከጉባዔተኛው ተነስተው በሚመለከታቸው አካላት ምላሽና ማብራሪያ ተሰጥቶባቸዋል።

ጉባዔው በውሎው የከተማ አስተዳደሩ ፍርድ ቤትና ምክር ቤት የ2O15 አፈፃፀም ሪፖርት እንዲሁም የ2O16 ዕቅድ ገምግሟል።

በመጨረሻም ለ2O16 የስራ ዘመን ማስፈፀሚያ 6 መቶ 2O ሚሊዮን 5 መቶ 93 ሺህ 1 መቶ 53 ብር በጀት በማጽደቅ ጉባዔው ተጠናቋል።

አንድ_ሆነን_እንስራ_ኢትዮጵያ_ታሸንፍ❗️

Previous የጉራጌና የኦሮሞ ህዝቦች የቆየ የእርስ በርስ ግንኙነት የበለጠ ለማጠናከር በልማቱ ስራም በትኩረት እንደሚሰራ የኦሮሚያ ክልል ርእሰ መስተዳድር ፕሬዝዳንት አቶ ሽመልስ አብዲሳ ተናገሩ።

Leave Your Comment

የቋንቋ አማራጭ

🇺🇸 English
🇪🇹 አማርኛ
🇪🇹 Afan Oromo