ከ50 በላይ የሚሆኑ የእንሰት ዝርያዎች አሉ። ከነዚህም 10 ለባህላዊ መድኃኒት አገልግሎት የሚውሉ የእንሰት ዓይነቶችና የሚሰጡት ጥቅም፦
1. አስታራ፦ ከእንሰት ዓይነቶች አንዱ ሲሆን ለስላሳ ባህሪይ አለው፡፡የአስታራ አሚቾ ሰውነት አንዲለሰልስ በማድረግ መግል አምግሎ ለማውጣት ያገለግላል፡፡
እንዲሁም የደም ስሮችንና አጥንት በማለስለስ የተዛነፉትን አንዲስተካከሉ ለማድረግ ይጠቅማል፡፡በተጨማሪም የሞቱ የደም ስሮችን ጭምር ህይወት እንዲዘሩ ያደርጋል፡፡ ጥጋት ላም የምትሰጠውን ወተት እንዲጨምር የአስታራ አሚቾና ኮባ ተቀቅሎ እንድትበላ ይደረጋል፡፡
ዕድሜው የገፋና የጠነከረ አስታራ ለሰውነት ጥንካሬ ወይም ሰውነት ለመጠገን ይጠቅማል፡፡
2. ቅብናር፦ እንደ አስታራ ሁሉ ለሰላሳ የእንሰት ዓይነት ሲሆን መግል ለማምገል ያግዛል፡፡
በተጨማሪም የወገብ ህመም የሚሰማው ሰው የቅብናር አሚቾ እንዲበላ ይደረጋል፡፡
3. ጫርቅማ፦ ይህ ደግሞ በጣም ለስላሳ ሲሆን የተለያዩ የአካል ክፍሎችን ይበልጥ እንዲለሰልሱ በማድረግ ከፍተኛ መግልና ቆሻሻ ከሰውነት እንዲወጣ ያደርጋል፡፡ ሆኖም ከሰውነት መውጣት የጀመረ መግልና ቆሻሻ ፈሣሽ በቀላሉ ሰለማይቆም አማራጭ ካልጠፋ በስተቀር ጥቅም ላይ እንዳይውል የዘርፉ ባለሙያዎች ይመክራሉ፡፡ በቀደምት ጊዜ የእንግዴ ልጅ ተቆርጦ የቀረበት ወይም አልወጣ ያላት ወላድ ሴት የዚህ እንሰት አሚቾ በልታ አልወጣ ያለውን የአንግዳ ልጅ ያስወጡ እንደነበረ ይናገራሉ፡፡
4. ጠርየ፦ ይህ ደግሞ እንደ ሌሎችም ለስላሳ ሲሆን በብዛት ጥቅም ላይ የሚውለው ጥጃ በሆድዋ የሞተባት ላም የሞተውን አካል እንድትገላገልና ጥጋት ላም የምትሰጠው የወተት መጠን እንዲጨምር ለማድረግ ያግዛል፡፡

5. ስንወት፦ በሰውነት ውስጥ እሾህ ወይም ስንጥር ወደ ስጋ ጠልቆ በሚገባበት በሹል ነገር ተነቅሶ ሊወጣ ካልቻለ የስንወት አሚቾ ተበልቶ በቀለሉ እንዲወጣ ይረዳል፡፡
6.ጓርየ፦ ይህ የእንሰት ዝርያ ጠንካራ ሲሆን በ2 ዓመታት ዕድሜ የሚገኝ የጓርየ አሚቾ የተለየዩ የሰውነት ክፍሎች ጥንካሬ እንዲያገኝ ይጠቅማል፡፡ የተጎዳ ስጋ፣ አጥንት፣ የደም ስሮችና ቁስል ለመጠገን ያገለግላል፡፡
7. ደሬ፦ እንደ ጓርየ ሁሉ ለጥንካሬ የሚያገለግል ሲሆን የተጎዳ የሰውነት ክፍል ይበልጥ እንዲጠነክርና እንዲጠግን ያደርጋል፡፡ከጥንካሬው ብዛት ጽንስ ሊያስወረድ የሚችል በመሆኑ እርጉዝ ሴቶች እንዳበሉት ይመከራል፡፡
8. ደሟነጀት፦ በወፍ በሽታ (ቆየ) የታመመ ሰው ከህመሙ እንዲያገግም ያደርጋል፡፡
9. አሻቅጥ፦ የወገብ ህመም ላመመው ሰው የሚታዘዝ የእንሰት ዓይነት ነው፡፡ የአሻቅጥ አሚቾ በጥሬው በወገቡ የተደገፈ ህመምተኛ ጭምር ህመሙ አንደሚቀንስለት ይነገራል፡፡
10. አጋዴ፦ በሚይገኝበት ወቅት ሰውነት ለማጠንከር ወይም ለመጠገን ይረዳል፡፡ እንግዲህ እነዚህ የእንሰት ዓይነቶች በስፋት ጥቅም ላይ የሚውሉት ይሁኑ እንጂ ሌሎችም ተጨማሪ የእንሰት ዓይነቶችም መኖራቸው መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡
በአጠቃላይ የእንሰት አሚቾ በባህላዊ መድህኒትነት ከማገልገሉም በላይ ለቡና ቁርስና እንዳስፈላጊነቱ ደግሞ እንደ አማራጭ ምግብ መጠቀም ይቻላል፡፡ በተለይ ድንገተኛ እንግዳ ተቀብሎ ለማስተናገድ ፈጥኖ ደራሽ ምግብ ነው፡፡ የሰውነት ጥንካሬ የሚሰጡ የእንሰት ዝርያዎች በማንኛውም ሁኔታ የተጎዳ ሰውነት ለመጠገን አስፈላጊ በሆነበት ወቅት ሁሉ በመመገብ ሰውነት መጠገን ይቻላል።

